“ለገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንድረስላቸው›› በሚል መሪ መልእክት ሐዋርያዊ ጉዞ ተካሄደ::

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ 

 

ታኅሣሥ 26 ቀን 2007 ዓ.ም.

20153 1 በማኅበረ ቅዱሳን አዳማ ማዕከል፣ የደብረ ዘይት ወረዳ ማዕከል ‹‹ለገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንድረስላቸው›› በሚል መሪ ቃል ምዕመናንን ያሳተፈ ሁለተኛውን ሐዋርያዊ ጉዞ ታህሳስ 26 ቀን 2007 ዓ.ም በጠንቁ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካሄደ፡፡


20153 2 ከ1,000 በላይ የቢሾፍቱ ከተማና አካባቢዋ ምዕመናን ተሳታፊ የሆኑበት ጉዞ የተካሄደው በምሥ/ሸዋ ሀ/ስብከት፣ በአድአ ወረዳ ቤተ ክህነት ከዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ተራራ ሥር የጠንቁ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በጉዞው የአድአ ወረዳ ሊቀ ካህናት መ/ፀ/ቀሲስ እንዳል ሐረገወይንና ሠራተኞች፣ የቢሾፍቱ ከተማ የስምንቱም አብያተ ክርስቲያናት ካህናት እና እንዲሁም ለቤተ ክርስቲያኒቱ አጎራባች የሆኑ አምስት የገጠር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአዳማ ማዕከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎትና የቅዱሳት መካናት ክፍል፣ የሞጆና ጨፌ ወ/ማዕከል፣ የዱከምና አዱላላ ግንኙነት ጣቢያዎች፣ የሰ/ት/ቤት ተወካዮችና ከ30 በላይ በጎ አድራጊ ማኅበራት በመርሃ ግብሩ ላይ ተሳታፊ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡


የደብረ ዘይት ወረዳ ማዕከል ሰብሳቢ አቶ ሀብታሙ ዘውዴ ስለ ጉዞውና ስለ ጉባኤው ሲገልጹ “ ሐዊረ ሕይወት ስናደርግ ይህ ሁለተኛችን ነው፡፡ ወደ ጠንቁ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ጉዞ የተደረገበት ዋነኛው ምክንያት ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑትን ምእመናን ለማስተማር፣ ለማበረታትና ለቤተክርስቲያኑ የሚያስፈልገውን እርዳታ ለማድረግ ሲሆን የጉዞው ተሳታፊ ምእመናንም የገጠሪቷን ቤተ ክርስቲያን በሚያስፈልገው ሁሉ እንዲረዱና ቃለ እግዚአብሔርን እንዲማሩ ነው፡፡”ብለዋል፡፡

 

አቶ ሀብታሙ አክለውም “ማኅበሩ በሚያደርገው ክትትልና ድጋፍ የምእመናኑ ቁጥር በየጊዜው ሊያድግ ችሏል፡፡ክትትሉም ጀኔሬተርና ድምጽ ማጉያ በማዘጋጀት፣ ከወረዳው ቤተክህነት ሠራተኞችና በተለይ ከሊቀ ካህናት መ/ፀ/ቀሲስ እንዳለ ሐረገወይን ጋር በመመካከር በኦሮምኛ ቋንቋ ማስተማር የሚችሉ ዲያቆናትና መምህራንን በየሳምንቱ በመመደብ የአካባቢው ምእመናን ስለተማሩ ቁጥራቸው አነስተኛ የነበረው ምእመናን ጸንተዋል፡፡ የሄዱትም በመመለስ ላይ ናቸው፡፡ ይህ ሐዊረ ሕይወትም እነዚህን ምእመናን ለማጠናከርን ለማበረታታት ያግዛል ተብሎ የተዘጋጀ ነው፡፡” በማለት ገልጸዋል፡፡


ከሀያ በላይ በሆኑ አውቶብሶች ጠንቁ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የደረሱት ተጓዦች አነስተኛዋን ቤተክርስቲያን ከተሳለሙ በኋላ የእለቱ ጉባኤ በጸሎት ተጀምሯል፡፡መዝሙሮችና ግጥም በወረዳ ማእከሉ መዘምራን ፣ ትምህርተ ወንጌል በሁለት ክፍል በአማርኛና ኦሮምኛ ቋንቋ በሊቀ ልሳናት ቀሲስ ከፍያለው ጥላሁን እና በዲ/ን ኃይለሚካኤል ተሰጥቷዋል፡፡


20151 የአካባቢው ምዕመናን ከወረዳ ማዕከሉ ጋር በመሆን ምግብ በማዘጋጀት፣ ድንኳኖችን በመትከል በተለይ መሬቱን ቆፈሮ በማስተካከል ዘመናዊ የጉባኤ አዳራሽ መስሎ የጉባኤው ታዳሚዎች ተመችቷቸው ጉባኤውን እንዲከታተሉ አስችሏል፡፡
በእለቱ 36(አባቶች፣እናቶች ወጣቶች፣ህጻናት) ቤተክርስቲያናቸውን ትተው የሄዱ ምእመናን ተመልሰው የቄደር ጥምቀት፣ ከቤተክርስቲያን ልጅነትን የምእመናንን አንድነትን የፈለጉ ምእመናን የቤተክርስቲያንን ትምህርት በወረዳው ቤተክህነትና በማኅበሩ ጥረት በመጠመቅ የሥላሴ ልጅነት አግኝተዋል፡፡


ስለጉባኤው ያነጋገርኳቸው የአካባቢው ነዋሪና የጠንቁ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ሊቀመንበር አቶ ገመቹ እንደገለጹት “እባካችሁ እውቀት የለንም አስተምሩን፡፡ መንገዱን አሳዩን፡፡ እድሜ ሰጥቶኝ ይህንን ጉባኤ ለማየት ስላበቃኝ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡”ብለዋል የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ምትኩ ታደሰና ወ/ሮ አይናለም ሸንቁሬ ስለጉባኤውና ስለጉዞው ሲገልጹ“ ሁሌ ቢኖር ጥሩነወ፡፡እንዲህ ዓይነት ጉዞ ያንጻል ፡፡ ልምድ ያካፍላል፡፡ የገጠር አብያተ ክርስቲያነትን ለመርዳት ያስችላል፡፡ወደፊትም ይቀጥል ብለዋል፡፡”

በመጨረሻም ለሁለት አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ አልባሳት በማኅበሩ የተበረከተ ሲሆን ከተጓዞች የተሰበሰበ 24000 ለጠንቁ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተበርክቷል፡፡

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1677-2015-01-05-08-57-14