መንክር ስብሐተ ልደቱ፤ የመወለዱ ምሥጢር ድንቅ ነው

መንክር ስብሐተ ልደቱ፤ የመወለዱ ምሥጢር ድንቅ ነው አትም ኢሜይል

«እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሴትን እናድርግ፤ በእርስዋም ደስ ይበለን፡፡» መዝ. 117·24 ይህች ዕለት ዕለተ ኃይል፣ ዕለተ አድኅኖ፣ ዕለተ ብሥራት፣ ዕለተ ቅዳሴ፣ ዕለተ ልደት፣ ዕለተ አስተርዕዮ ናትና ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ ከአብ ባሕርይ ዘእምባሕርይ፣ አካል ዘእምአካል፣ የተወለደ ወልድ ዋሕድ ኋላም ከድንግል አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ በዚህች ዕለት በኅቱም ድንግልና ተወልዷልና ዕለተ ኃይል ትባላለች፡፡ መላእክት በጎል ተጥሎ፣ በጨርቅ ተጠቅልሎ አይተው ስብሐት ለእግዚአብሔር ብለው አመስግነውበታልና ዕለተ ቅዳሴ፣ መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን በጎል ተገኝቶበታልና ዕለተ አድኅኖ፣ ቅዱስ ገብርኤል እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ብሎ ተናግሯባታልና ዕለተ ብሥራት ትባላለች፡፡ «እግዚአብሔርም አለኝ አንተ ልጄ ነህ እኔም ዛሬ ወለድሁህ» መዝ 2·7 በተዋሕዶ፣ በቃል ርስትነት ተብሎ የተነገረለት ቀድሞ ብቻውን እግዚአብሔር ከብቻው እግዚአብሔር እንደተወለደ፣ በኋለኛውም ዘመን ብቻውን የሚሆን የእግዚአብሔር ልጅ ብቻዋን ከምትሆን ከዳዊት ልጅ ተወለደ፡፡

በመጀመሪያ የማይታይ እሱ ከማይታየው ተወለደ፤ በኋላም የማይያዝ የሕይወት እስትንፋስ ከምትዳሰስ ሥጋ ተወለደ፡፡
በመጀመያ የአኗኗሩ መጀመሪያ ሳይታወቅ ተወለደ፤ በኋላም የዘመናት ፈጣሪ ዓመታትን የሚወስን እርሱ ዕድሜዋ ዐሥራ አምስት ከሆነ ከታናሽ ብላቴና ተወለደ፡፡
የመጀመሪያ ልደቱን ምሥጢር፣ የኋለኛ ልደቱንም ድንቅ በማድረግ ተወለደ፡፡
በቅድምና የነበረው የአብ አካላዊ ቃሉ በምልዓት ሳለ ተፀነሰ፤ በጌትነቱ በጽርሐ አርያም ሳለ ሰው ሆነ፤ ማኅተመ ድንግልናን ሳይለውጥ የእኛን ባሕርይ ተዋሕዶ ተወለደ፡፡
የሰውን ልጅ በጥንተ ተፈጥሮ የፈጠረ የእግዚአብሔር አብ ልጅ እግዚአብሔር ወልድ አሁን ደግሞ በሐዲስ ተፈጥሮ ለመፍጠር ሰው ሆኖ ተወለደ፡፡ «ሰው ሆይ አስተውል እሱን አስመስሎ ይወልድህ ዘንድ አንተን መስሎ ተወለደ ስለዚህ ነገር ቅዱስ ጳውሎስ መላእክትን የተቀበለ አይደለም፤ የአብርሃምን ዘር ከፍ ከፍ አደረገ እንጂ» እንዳለ ዕብ 2·16 የሰውን ልጅ ክብር ወደ ቀደመ ማንነቱ ለመመለስ እንዲህ ባለ ድንቅ ልደት ዛሬ ተወልዷልና ዕለተ ልደት ትባላለች፡፡
«በሀገራቸው ትንቢት የተነገረላቸው በዕብራይስጥ ልሳንም የተጻፈላቸው እስራኤል ምንም ባያውቁህ ከዓለም አስቀድሞ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ ደግሞ ከዳዊት ዘር ከምትሆን ቅድስት ድንግል ተወልደህ የሰው ልጅ መባልህን አወቅሁ» ማቴ 16·13-18
ትንቢቱስ ምን ነበር እግዚአብሔር፤ አዳምን ከአራቱ ባሕርያት ፈጥሮ ከእንስሳት ከአራዊት ለይቶ በነባቢት ነፍስ አክብሮ ልጅነትን ሰጥቶ ሥራ ሠርቶ ሊጠቀምበት መንፈሳዊ ዕውቀትን አድሎ በአርአያው በአምሳሉ የፈጠረው ነውና የባሕርዩን በጸጋ ሰጥቶ የሁሉ ገዥ አድርጎ በገነት ሹሞ አኖረው፡፡ ነገር ግን የገዥና የተገዥ ምልክት የምትሆን ዕፀ በለስን እንዳይበላ አዘዘው፡፡ ይኸውም የንፍገት አይደለም፤ ከሹመቱ እንዳይሻር፣ ከልዕልናው እንዳይዋረድ፣ ከልጅነት እንዳይወጣ፣ ክብርን እንዳያጣ ነው እንጂ፡፡ ሆኖም ግን የራሱን ክብር ልዕልና በራሱ ያጣ ዲያብሎስ በአዳም ክብርና ልዕልና ቀና፡፡ በሥጋ ከይሲ ተሠውሮ በሽንገላ መጣ፡፡ ክፋትን በተመላ ደስ የሚያሰኝ በሚመስል አነጋገር የሞት ሞት የምትሞቱ አይምሰላችሁ የዕፀ በለስ ፍሬ ብትበሉ የአምላክነት ዕውቀት ይሰጣችኋል፡፡ ክፉውንም ደጉንም ታውቃላችሁ፤ አሁን ካላችሁበት ክብርና መዓርግ ከፍ ትላላችሁ በማለት አታለላቸው፡፡ እነርሱም እውነት መሰላቸው፡፡ ከፈጣሪያቸው ትእዛዝ ወጡ፡፡ ራሳቸውን አጥፊ ሆኑ፤ የቀደመ ማንነታቸውን አጥተው ኃሣር፣ መርገም፣ ድንጋፄ፣ ረዓድ ወደሚበዛበት፣ ክፉና መልካም ወደሚሠራበት፣ ቢያገኙት ቁንጣን፣ ቢያጡት ቀጠና ወደ ሆነበት ዓለም ወረዱ፡፡ ቢሆንም ግን አዳም በፍታዊነቱ አንጻር መሐሪነቱን ተረድቶ በደሉን በማመን አዘነ፤ አለቀሰ፤ በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና ጸዋትወ መከራውን አይቶ አዘነለት፡፡ የሚድንበትን ተስፋ ትንቢት ሰጠው፡፡ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ከዚህም አያይዞ ከልጅ ልጁ ተወልዶ የሚያድነው ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል መሆኑን፣ እርሱን ለማዳን ስሙን ባሕርዩን ገንዘብ የሚያደርገው ወልድ ኢሳ 9·6 መሆኑንም ጨምሮ ነግሮታል፡፡ ዘፍ 3·22 ይህ የሚፈጸምበትን ቀጠሮም አስረድቶታል፡፡ ገላ 4·4 ከዚያ ቀጥሎ በየጊዜው ለተነሡ ልጆቹ ትንቢቱን በማስነገር፣ ምሳሌውን በማስመሰል፣ እስከ ጊዜው ደርሷል፡፡ ለዚህም ነው በዘመነ አበው የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ ተብሎ የሃይማኖት መሠረት ለሆነው ለአብርሃም የተነገረው ዘፍ 22·18
በዘመነ መሳፍንትም አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱንም ታደምጣለህ ተብሎ በሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ በሙሉ አዋጅ ታውጇል፡፡ ዘዳግ 18·15
በዘመነ ነገሥት ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ ብሎ ለዳዊት የገባው ልዩ ቃል ኪዳን አለ፡፡
ስለዚህ እወቅ አስተውልም ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ተብሎ በነቢዩ ዳንኤል 9·25 ተነግሯል፡፡
ያዕቆብም በምርቃት የገለጸው ልጆቹን ለእያንዳንዳቸው እንደሚገባቸው የጸጋ ሀብት በረከታቸውን ባሳየ ጊዜ የይሁዳን መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፤ ግዛትም ከወገኑ ገዥ የሆነው እስኪመጣ ድረስ እርሱም የአሕዛብ ተስፋቸው ነው፡፡ ዘፍ 49·10 ከይሁዳ ወደ ዳዊት እየቀረበ ሲመጣም እርሱም አባቴ አንተ ነህ ይለኛል እኔም በኩር አደርገዋለሁ፡፡ መዝ 88·20 1ሳሙ 16·1-13 በማለት ሥጋ (አካለ) ዳዊትን በተለየ መልኩ እንደመረጠው ፈጣሪው ሲሆን ልጁ ለመባል እንደወደደ እየገለጠው እያቀረበው መጣና ወደ ልጁ አለፈ፡፡
ዳዊትንም ልጁን ለዚህ ታላቅ ምሥጢር እንዲያዘጋጅ በትንቢት አነሣሣው፡፡ እርሱም ልጁን እንዲህ አላት፤ «ልጄ ሆይ የምልሽን ስሚ፤ እይ፤ ጆሮሽንም ወደ ምሥጢሩ ቃል አዘንብይ፤ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ፤ ያለምንም የልብ መከፈል ራስሽን ለርሱ ስጪ፤ ንጉሥ ውበትሽን ይኸውም ንጽሕናሽን፣ መዓዛሽን፣ ቅድስናሽን ወዷልና፡፡ እርሱ ሌላ አይደለም፤ ለታላቁ ምሥጢር የመረጠሽ ጌታሽ ነውና፡፡» መዝ 44·10-12 አላት፡፡ ደስ በሚያሰኝ የተስፋ ቃል ትንቢቱን ተናገረ፡፡ እርሱም ይሁንልኝ ብላ የአባቷን ምክር ተቀብላ የአምላክ እናት ለመሆን በቃች፤ ትንቢቱም ደርሶ የገባውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ ወደደ፡፡
ደም ግባቷን በወደደ ጊዜም በጽርሐ አርያም እናት ትሆነው ዘንድ ወደ ሰማይ አላሳረጋትም፤ እርሱ ራሱ ወደእርሷ ወረደ እንጂ፡፡ በዚያ ትፀንሰው ዘንድ በኪሩቤል ሠረገላ ላይ አላስቀምጣትም፤ ናዝሬት በተባለች በገሊላ ሀገር ሳለች እርሱ ራሱ በማሕፀኗ አደረ እንጂ፡፡ ገብርኤልንም ዘጠኝ ወር በማሕፀኗ እንድትሸከመኝ ወደዚህ አምጣት አላለም፤ እርሱ ራሱ ትሕትናዋን ተሳተፈ እንጂ፡፡ ይልቁንም መልክተኛውን በትንቢት ወደ መረጣት የዳዊት ልጅ ላከ፡፡ እርሱም ደስ ያለሽ ሆይ ደስ ይበልሽ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው፤ እነሆ ኢሳይያስ ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ትወልዳለች እንዳለ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም አማኑኤል ትይዋለሽ፤ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋን፣ ከነፍሳችን ነፍስ ነስቶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ፤ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሆነውም ኢየሱስ ተባለ፤ ትርጓሜውም ወገኖቹን የሚያድናቸው ማለት ነው፡፡ ይህ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ የሆነ ሳይሆን ከጥንቱ ሲነገር ሲያያዝ የመጣ ነው አላት፡፡ እርሷም እንዲህ ያለ ሰላምታ እንደምን ይቀበሏል አለች፡፡ በትሕትና መልአኩም በእግዚአብሔር ዘንድ የእናትነት ባለሟልነትን አግኝተሻልና ደስ ይበልሽ፤ የምትወልጅውም የልዑል እግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ይባላል፤ እግዚአብሔር የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ወገን ለዘለዓለም ነግሦ ይኖራል፡፡ ለጌትነቱ ፍጻሜ የለውም አላት፡፡ ነገሩስ መልካም ነበር፤ ነገር ግን ወንድ ሳላውቅ መፅነስ መውለድ እንደምን ይሆንልኛል? በውኑ ምድር ያለ ዘር ታፈራ ዘንድ ሴት ያለወንድ ትፀንስ ዘንድ ይቻላልን? ሴት ያለ ወንድ ዘር መውለድ ከዚህ በፊት አልሆነምና አለችው፡፡
እውነት ነው ከዚህ በኋላም አይሆንም ነገር ግን ያንች ፅንስ እንደ ሌሎች ፅንስ አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤ ኃይለ ልዑል ወልድ ሥጋሽን ይዋሓዳል፤ ለሱ የሚሳነው ነገር የለም፤ ሁሉን ማድረግ ይቻለዋል አላት፤ እርሷም ጊዜ በፍጹም እምነት ቃለ ብሥራቱን ተቀብላ አቤቱ እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋዩ ነኝ እንደ ቃልህ ይደረግልኝ ባለች ጊዜ ፈቃዷን ምክንያት አድርጎ የዓለሙ ሁሉ መድኃኒት የሚሆን ዋሕድ ቃለ እግዚአብሔር በማሕፀኗ ተቀርፆ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን የማይወስነው በማሕፀኗ ተወስኖ ሊወለድ የማይቻለው ተወለደ፡፡ በሰው ዘር ያልሆነ ነገር ግን እንደ ሰው የሆነውን ልደቱን እናምናለን፡፡
አምላክ ሲሆን መወለዱን፣ ወደዚህ ዓለም መምጣቱን፣ ከረቂቃን የረቀቀ ድንቅ ነው ከድንግል መወለዱ ፍጹም ሰው ቢሆንም ያለ ዘር በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ በኅቱም ድንግልና መወለዱ ግን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በመሆኑ ፍጹም አምላክ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህ ልደት እጅግ አስደናቂ ልደት ነው፡፡ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና መወለድ ለዘለዓለም አዲስ ሥራ ቢሆንም በድንግልና መጸነሱም ሆነ መወለዱ በእርሱ ለእርሱ ብቻ እንጂ በማንም ሥልጣን ለማንም እስካልሆነ ድረስ ከማድነቅ ውጪ እንዴት ሊሆን ቻለ ማለት አይገባም፡፡ ይልቁንም ልደቱን በመመራመር ማወቅ አይቻልም በማመን እንጂ፤ እነዚህም ሁለት ልደታት ናቸው፡፡
1. ከዘመናት በፊት ዓለማት ሳይፈጠሩ ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ የተወለደው፡፡ መዝ 10·3 ይህ የመጀመሪያው ልደት ሲሆን፤
2. በኋላኛው ዘመን ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ በድንግልና የተወለደው ሁለተኛ ልደት ነው፡፡ ኢሳ 7·19 9·6 ማቴ 1·22-23 2·1 ገላ 4·4 ይህን ድንቅ ምሥጢር ሊቁ እንዲህ በማለት ይገልጠዋል፤ «አቤቱ ሆይ በአኗኗርህ የአብ ልጅ፣ በሰውነትህ የድንግል ልጅ፣ በመለኮትህ የአብ ልጅ፣ በትስብእትህ የሰው ልጅ፣ ለወለደህና ለወለደችህ አንድ ልጅ እንደሆንህ አመንሁብህ፡፡ አቤቱ ጌታዬ የላይኛው ቀዳማዊ ልደት ሌላ፣ የታችኛው ሁለተኛው ልደት ሌላ፣ ሰማያዊ ልደት ሌላ፣ ምድራዊ ልደት ሌላ፣ የልዕልና ልደት ሌላ፣ የትሕትና ልደትህ ሌላ፣ የፊተኛው ልደትህ ከሕይወት እሳት የተገኘ የሕይወት እሳት፣ የኋለኛው ልደት ከሴት የተወለደ አካላዊ ቃል የፊተኛውን ፈለግሁት አላገኘሁትም፤ የኋለኛውን አሰብሁት አደነቅሁት፤ የፊተኛውን ሳልደርስበት አመሰገንሁት፤ የኋለኛውን በአብራከ ልቡናዬ ሰግጄ እጅ ነሣሁት፡፡ የፊተኛው ልደት በኋለኛው ልደት ታወቀ ተረዳ፡፡ የመለኮት ወገን በድንግል ወገን ተመሰገነ፡፡ ከድንግል ከተወለድህ ወዲህ ከአብ የመወለድህ ሃይማኖት ተገልጸልን፤ ከድንግል መወለድህን በሚናገር ትንቢት ከአብ መወለድ ተረዳ፡፡ ስለዚህ ባለመጠራጠር አመንሁ» ይላል አባ ጊዮርጊስ፡፡
ምን ጊዜም የልደቱ ነገር ድንቅ ምሥጢር ነው፤ ቅዱስ ኤፍሬም እንደሚለው ሰው የሆነ እርሱን አምላክ እንደሆነ በተረዳ ነገር አውቀነዋልና ልዩ ከሆነች ድንግል ማርያም ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይረቅ ረቂቅ ነው፤ ድንቅ ነው፡፡ ቃልን ወሰነችው፤ ልደቱንም ዘር አልቀደመውም፡፡ በመወለዱም ድንግልናዋን አለወጠም፤ ቃል ከአብ ያለ ድካም ወጣ፤ ከድንግልም ያለ ሕመም ተወለደ፡፡ ለዮሴፍ የታየው መልአክም ከእርሷ በመንፈስ ቅዱስ የሚወለደው ያለመለወጥ ሰው የሚሆነው የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ይኸውም ከባሕርያችን እርግማንን የሚያጠፋልን ያለወንድ ዘር የተወለደልን፣ አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ የተባለውም እነሆ ዛሬ ከቅድስት ድንግል ነፍስን ሥጋን ነሥቶ በተዋሕዶ በተገለጠ ጊዜ ተፈጸመ፡፡
አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ተመኘ፤ ቀኔንም /ልደቴን/ አይቶ ተደሰተ ተብሎ የተተነበየለት ዕለተ ምሥጢር ዕለተ ልደት ይህች ናት፡፡ እኛም ያየናት የድኅነት መጀመሪያ የዕለታት በኩር እንደሆነች ተረድተን የምናከብራት ደስታችንን የምንገልጽባት ይህች ዕለት ዕለተ አስተርዕዮ ናት፤ የማይታየው የታየባት፣ የማይዳሰሰው የተዳሰሰበት፣ የማይያዘው የተያዘባት፣ የማይታወቀው የታወቀባት፣ በትንቢት መነፅር አበው ያዩት ረቂት ብርሃን በአካል የተገለጠባት የአብንም ወላዲነት የተረዳንባት ዕለት ናት፡፡ በዚያ በአባቱ ቀኝ ሳለ በዚህ ከእናቱ ዕቅፍ ውስጥ ታየ፣ በዚያ ተሸካሚዎቹ እሳታውያን የሚሆኑ አራቱ እንስሳ ናቸው፡፡ በዚህም የተሸከመችው የፀሠራ አምስት ዓመት ብላቴና ድንግል ማርያም ናት፡፡ በዚያ ያለ እናት፣ አባት አለው፤ በዚህም ያለ ምድራዊ አባት፣ እናት አለችው፡፡
በዚያ በጽርሐ አርያም የሚደነቅ ከማይመረመር ከማይታይ አብ የመወለድ ምስጋና አለው፤ በዚህም በቤተ ልሔም የሚደነቅ ከድንግል የመለወድ ምስጋና አለው፡፡
በዚያ ኪሩቤልና ሱራፌል ከግርማው የተነሣ ይንቀጠቀጣሉ፤ በዚህ ግን ድንግል አቀፈችው፡፡ ሰሎሜም አገለገለችው፡፡ በዚያ የእሳት ዙፋን አለ፤ በዚህም የድንጋይ በረት አለው፤ በዚያ የትጉሃን ሥፍራ በሰማያት ያለች ኢየሩሳሌም አለችው፤ በዚህም የእንስሳት ጠባቂዎች ማደሪያ በዓት አለችው፡፡ በዚያ ገብርኤል በፍርሃት ይቆማል፤ በዚህም በሐሤት የምሥራች ይናገራል፡፡
በዚያ የእሳት ወላፈን ከአዳራሹ ይወጣል፤ በዚህም አህያና ላህም በእስትንፋሳቸው አሟሟቁት፡፡
እነሆ ከሰማይ ትጉሃን ይልቅ የሰው ልጅ ከበረ፤ እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም ተወልዷልና፡፡ አንዱ የመወለዱ ምሥጢርም ይህ ነው፤ የሰውን ልጅ ከወደቀበት አንሥቶ በክብር ሰገነት ላይ ለማኖር የሰው ልጅም በጥንተ ተፈጥሮ ካገኘው ክብር የዛሬው በአዲስ ተፈጥሮ የሚያገኘው ክብር በልጧልና፡፡ የፊቱ በአምሳል በመፈጠር የተገኘ ነው፤ የአሁኑ ግን በተዋሕዶ በመወለድ የሚገኝ ነውና፡፡ የፊተኛው ሥጋ በጸጋ ከብሮ የተገኘ ነበር፤ አሁን ግን ሥጋ የባሕርይ አምላክ ሆኖ የተገኘ ከብር ነውና፡፡ የፊቱ ያለ ባሕርይ (በጸጋ) መከበር ነበር፤ ዛሬም በራስ ባሕርይ መከበር ነውና፡፡
ከአቂበ ሕግ በመውጣት ከወረደበት በታች የወረደበት ውርደት የለም፤ ዛሬም በተዋሕዶ በተደረገው ምሥጢር ከከበረበት በላይ ክብር የለም፤ በልዑል ዙፋን እስከመቀመጥ ደርሷልና፡፡
ትናንት ያልነበረ ሰውነት ከዘመን በኋላ የተገኘ ሲሆን፣ መለኮትን በመዋሓድ ሁሉን ግዙ ተብሎ ጥንት በጸጋ ከተሰጠው ግዛት በላይ ግዛቱ ድንበር የማይመልሰው ዘመን የማይለውጠው ከምድር እስከ ሰማይ የመላ ግዛት ሆነለት፡፡ መለኮት ወደሱ የመጣበት አመጣጥ ድንቅ የወደደበት ፍቅር ልዩ፣ በባሕርይ መወለዱም ዕፁብ ነውና ይህም ልደቱ ያለ ዘር የተደረገ ነው፡፡ ስለምን ቢሉ ቀዳማዊ ልደቱ የሚገለጥበት ነውና አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ያለአባት ያለዘር መወለዱ ቅድመ ዓለም ያለእናት ለመወለዱ ምሥክር መታወቂያ ነውና፡፡ ለዚህም ነው የመጀመሪያው ልደት በሁለተኛው ልደት ታወቀ የሚባለው፡፡ የሁለተኛው ልደት ክብርና ምሥጢርም ከአእምሮ በላይ በመሆኑ በመጀመሪያ ልደት ታወቀ ተረዳ፡፡ ድንቅ የሚሆን ልደቱም በምድር ላይ አባት ስለሌለው ሰው የመሆን መንገድ የጐደለው አይደለም፤ ብቻዋን ከምትሆን ከድንግል ፍጹም ሰው ሆኖ ተወለደ እንጂ ከአዳም ጐን እናት ሳይኖራት ፍጽምት ሴት እንደወጣች ፍጹም ሰው ሆነ፡፡ ማቴ 2·1-12 ሉቃ 2·8-16
የአብ ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው በሆነ ጊዜ የሕፃናትን ጠባይ ሳያስቀር የሰውነትን የጠባይ ሥርዓት እየፈጸመ ከዕለተ ፅንሰ ጀምሮ እስከ ዕለተ ልደት ድረስ በየጥቂቱ በማሕፀነ ማርያም ውስጥ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ቆይቶ ሕፃናት ሲወለዱ የሚሰማቸው ሳይሰማው ተወለደ፡፡ ሲወለድም በግብረ መንፈስ ቅዱስ በድንግልና እንደተፀነሰ በድንግልና ተወለደ እንጂ እናቱንም የድንግልና መለወጥ፣ በወሊድ ጊዜ ጭንቅና ምጥ አላገኛትም፡፡ ሕዝ 34·1 የመውለዷ ክብር ገናንነትም ከአእምሮ በላይ ነው፤ ይህ ተብሎ ሊነገር አይችልም፤ ያለ ምጥ ወልዳዋለችና፡፡
የዲያብሎስና የተከታቹን ሥነ ልቡና የሰበረ በፍርሃት እንዲዋጡ ማንነታቸውን እንዲያጡ ያደረገው አስደናቂው ልደት ጌታ በቤተ ልሔም ሲወለድ ቤተ ልሔም በብርሃን ተከባ፣ በመላእክት ምስጋና ደምቃ፣ በምሥራች ተመልታ ባየ ጊዜ የሰው ልጅ ጠላት ዲያብሎስ ይህን የልደት ምሥጢር ለማወቅ ለመመራመር ወደ ላይ ወደ ዐየር ወጣ፤ ከመሬት በታች ወደ አለው አዘቅት ወረደ፤ ዓለምን በሙሉ ዞረ፤ ግን ሊያውቅ አልቻለም፡፡ ባለማወቅ ሠወራቸው ተብሎአልና መርምሮ ማወቅ ባይቻለው የፍርሃት ጥርጥር መጠራጠር ጀምረ እንዲህ በማለት፤ የኢሳይያስ ድንግል የድንግልና ልጇን ወለደች፤ ተአምረኛው ሙሴ ሲወለድ እንዲህ ያለ ችግር አልገጠመኝም ብዙ ክብር ያላቸው ነቢያት ተወልደዋል፤ እንደዚህ ማንነቴን የሚያሳጣ ከዕውቀቴ በላይ የሆነ ችግር አልገጠመኝም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ዓለምን በሙሉ ዞርኳት፤ ይልቁንም ቤተ ልሔምን፡፡ ነገር ግን በእሷ የተደረገ የዚህን ልደት ምሥጢር ተመራምሬ ልደርስበት አልቻልኩም፡፡ ድካሜም ውጤት አልባ ሆኖአል ብሎ ወደ ወገኖቹ ቢመለስ በግምባራቸው ፍግም ብለው ወድቀው አገኛቸው፡፡ ለጊዜው እነሱን አይዟችሁ መንግሥቴ ከእኔ አታልፍም አላቸው፡፡ ከተደረገው ተአምራት ሁሉ በላይ ተአምር ቢደረግም አልፈራም ነበር፡፡ ትንቢቱ ቢደርስ ድንግል ልዑሉን ብትወልድ ይሆናል እንጂ እንዲህ ያለ ኃሣርና ውድቀት ያገኘን ምን አልባት ቤተ ልሔም አምላክ ተወልዶብሽ ይሆን ብሎ ተስፋ ባለመቁረጡ ተመልሶ ሄደ፡፡ መላእክት በአንድነት ሆነው በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እነሆ በምድር ላይ ለሰው የሰላም መሠረት ተጥሏልና እያሉ ሲያመሰግኑ፣ ደግሞ መልአኩ ለእረኞች እነሆ ለእናንተ ደስታ የሚሆን ምሥራች እነግራችኋለሁ፡፡ የዓለም መድኃኒት የሚሆን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት ባሕርይ በዳዊት ሀገር ተወልዷልና፤ ምልክቱም አንዲት ድንግል ልጅ ሕፃኑን በክንዷ ታቅፋ ታገኛለችሁ ሲል ሰምቶ በሐዘን ላይ ሐዘን ተጨመረበት፡፡ ቢሆንም ግን እርግጡን ለማወቅ የልደት ዘመን መቼ እንደሆነ ለመረዳት የነቢያትን መጻሕፍት ትርጓሜ ወደሚያውቁ ወደ አይሁድ ሊቃውንት ዘንድ ፈጥኖ ሄዶ ስለ ክርስቶስ መወለድ አንሥቶ ያስረዱት ዘንድ አጥብቆ ጠየቃቸው፡፡ የጠየቃቸውን እንደማይሸሸጉት ተስፋ አድርጓልና እነሱም በይሁዳ አውራጃ በምትገኝ በቤተ ልሔም የዓለም መድኃኒት ይወለዳል ብለው ተናግረዋል ብለው መለሱለት፡፡ ሚክ 5·2 የዳንኤል ሱባዔስ ደርሷል? አላቸው፡፡ «አዎ» አሉት፡፡ «ይህ ሁሉ እንደደረሰ በምን አውቃለው?» አላቸው፡፡ የልደቱ መታወቂያ የጊዜው መድረስ የሚታወቅበት ከልደቱ ጋር ቀጠሮ ያለው ልደቱን የሚጠባበቅ ስምዖን የሚባል አለ፡፡ እሱን ጠይቀህ ተረዳ አሉት፡፡ ስምዖን ለልደቱ ምልክት የሆነበት ምክንያት ምንድ ነው? አላቸው፡፡ ለንጉሡ በጥሊሞስ መጻሕፍት ከእብራይስጥ ወደ ፅርዕ ሲተረጉም ኢሳይያስ እነሆ ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች ባለው የትንቢት ቃል በተሰነካከለ ጊዜ የእግዚአብሔርም መልአክ ሕፃኑን ሳታይ አትሞትም ብሎታልና ሉቃ 2·26 አሉት፡፡ ሒዶ አንተ የተባረክህ ሽማግሌ ተስፋ የምታደርገው መድኅን ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጫው ደርሷልን? አለው፡፡ አዎ መጥቷል፤ አለው፡፡ በምን አወቅህ? አለው፡፡ በኢሳይያስ ትንቢት በተሰነካከልኩ ጊዜ በሕማም ታሥሮ የነበረው እጄ ተፈትቷልና በዚህ አወቅሁ አለው፡፡ በመልክተኞቹ ይህን ከሰማ በኋላ እውነትም ዛሬ ገና የእኔ ክብር የሚዋረድበት፤ ያዋረድሁት አዳም ከእኔ ባርነት ነጻ የሚወጣበት ቀን ደርሰ አለ፡፡ የአዳም ልጅ ሆይ ጠላት ዲያብሎስ ላይጠቅመው ላይረባው ይህን ያህል ስለ ልደቱ ምሥጢር ለማወቅ አቀበቱን ከወጣ ቁልቁለቱን ከወረደ፣ ዓለምን በመዞር ከተንከራተተ፣ አንተማ ምን ያህል ልትደክም አይገባህ? የማንነትህ ህልውና ነውና የልደቱን ነገር ልታውቅ ይገባሀል፡፡ ግን በምርምር አይደለም፤ እንደ እረኞች በእምነት ነው እንጂ፡፡ እረኞች በምርምር ሳይሆን በምልክት ተረድተው ልደቱን አወቁ፤ አገኙትም፡፡ አንተም ከመጻሕፍት አንብበህ ከመምህራን ተረድተህ የእረኞች ምሥራች የእኔ ነው ብለህ ነው እንጂ በልደት የሠለጠነ አምላክ በጎል ተጥሎ፣ በጨርቅ ተጠቅልሎ፣ በግርግም ተኝቶ አይቶ ዲያብሎስ ፈራ፡፡ አዳም ግን የልዑልን ትሕትና አይቶ ኦ ወዮ ለዚህ ምሥጢራዊ ልደት አንክሮ ይገባል፤ መርምረው ሊያውቁት አይቻልምና፡፡ አምላኬ ለእኔ ሲል የተወለደው ይህ ልደት ብቸኛ ነው ብሎ አመሰገነ፡፡ ብቸኛ ያሰኘውም በዚህ ዓለም እናት አባት አንድ ካልሆኑ ልጅ አይወለድም፤ እሱ ግን ከአባት ያለ እናት ከእናት ያለ አባት ተወልዷልና፤ የዚህ ዓለም ልጅ በዘር በሩካቤ ይወለዳል፤ እሱ ግን ያለ ዘር ያለ ሩካቤ ተወልዷልና፡፡
የዚህ ዓለም ልጅ ልጅ ተብሎ ኑሮ የወለደ ጊዜ አባት ይባላል፤ እሱ ግን ለዘለዓለም ወልድ እየተባለ ይኖራልና፡፡
ይህች ዕለት ለፍጡራን የሚሆን ሁሉ ዕረፍት የሚሆን ወልድ ሰውነቱን በልደት የገለጠበት ዕለት ስለሆነች ፍጡራን ሁሉ መልካም ዜና ሰሙ፤ ደስም አላቸው፡፡ ደስታቸውንም ገለጡ፡፡ ሊቁ እንዳለው ሰው በመሆንህ ሥጋን በመዋሓድህ ወደዚህ ዓለም በመምጣትህ ፍጥረት ሁሉ ደስ አላቸው እንዳለ፡፡
መላእክት ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በድንግል እቅፍ አይተው ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ አሉ፡፡
ሰዎችም የፍጥረት ባለቤት እነሱን ለማዳን ልዑል ሲሆን በራሳቸው ባሕርይ በትሕትና ተወልዶ አይተው ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት አሉ፤ እንሰሳት አራዊት ለሰው በተደረገው ይቅርታና ክብር እስትንፋሳቸውን አምኀ አቀረቡ፡፡ ስሙን እየጠሩ ለዓለም መሰከሩ፡፡ ለምሳሌ ያህል ሚዳቋን ብንወስድ እንኳ ዮም ተወልደ መድኅነ ዓለም፤ ዮም ተወልደ ከሣቴ ብርሃን፤ ዮም ተወልደ ቤዛ ኵሉ ዓለም የዓለም መድኃኒት ዛሬ ተወለደ እያለች ስትዘምር ታይታለች፡፡ አስተዋይ አዕምሮ ካለ ይህ ድንቅ ምሥጢር ነው
ፊተኛ ልደቱ ፍጡራን የማያውቁት፣ በምሥጢር መሠወሪያ የተሠወረ ነው፡፡ ኋለኛ ልደቱ ግን ለእረኞች ተገለጠ፡፡ ለጥበብ ሰዎችም ታየ፡፡ በዓለምም ተሰማ፡፡ ልጄ ወንድሜ ሆይ ቃል /ወልድ/ በምድራችን ተሰማ፤ መታየቱም የታመነ ሆነ፡፡ በአባቱ መልክ /በአምላክነት ባሕርይ/ ተመላለሰ እንዳለ፡፡ መኃ 2·12-13 ጌትነቱን ለሚያምን ሁሉ አባቶቻችን በእሳት አምሳል ያዩትን እኛ ተገልጦ አየነው፤ ቃሉንም ሰማነው እያልን እንመሰክራለን፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋር ሰው ሆነም ስንል በፍጹም ተወሕዶ ነው፤ ተዋሕዶ ማለት አንድ መሆን መዋሐድ አለመለያየት፣ የማይታየው ከሚታየው፣ የማይወስነው ከሚወሰነው፣ ጋር አንድ ሆኖ ለዘለዓለም ለመኖር አካላዊ ቃል እግዚአብጠር ወልድ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በማሕፀነ ማርያም አድሮ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ መወለዱን ነው፤ ወንጌላዊው ዮሐንስም ቃል ሥጋ ሆነ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ ያለው ይህን ፍጹም ተዋሕዶ ነው፡፡ ይህም ተዋሕዶ አካላዊ መሆኑን ይገልጻል፤ ሰው ሆኖ ተወልዷልና፡፡
ስለዚህ በተዋሕዶ ለተፈጸመው ለልደት ምሥጢር አንክሮ ይገባል፡፡ ያለዘርዓ ብእሲ መፀነስ፣ ያለ ተፈትሖ መወለድ፣ ዘመን በማይቆጠርለት ሕፃን አፍ ከድንግል ጡት ወተት መፍሰስ፣ እግዚአብሔር ለመረጣቸው ለመቅደስ ካህናት ያልተደረገ ለከብት እረኞች ሰማያዊ ምሥጢር መገለጥ፣ ከሩቅ ምሥራቅ ተነሥተው የጥበበኞች በኮከብ እየተመሩ ወደ ቤተልሔም መሔድ፣ አንክሮ ይገባል፤ ከነገሥታት እጂ ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ መቀበልም ድንቅ ያሰኛል፡፡ በዚያ ሰማያውያን ካህናት በወርቅ ማዕጠንት ያቀረቡትን የዕጣን መዓዛ ይቀበላል፡፡ በዚህም ዛሬ ከሰብአ ሰገል ይህን ተቀበለ፤ መላእክትና እረኞች ዝማሬን፣ እንስሳት እስትንፋሳቸውን፣ ኮከብ ብርሃኑን አቀረቡ፡፡ እኛም ይህን ተረድተን አሕዛብ ሁላችሁ በእጃችሁ አጨብጭቡ፤ በደስታም ቃል ለእግዚአብሔር እልል በሉ፤ ስሙንም አመስግኑ፤ ለጌትነቱም ምስጋና አቅርቡ እንላለን፡፡ መዝ 65·1
በአዳም በደል ያልተጸጸተ በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ያልተደሰተ የለምና የዚህ ልደት ዓላማም ሰውን ከስሕተቱ መልሶ የእግዚአብጠር ለማድረግ ነው ዮሐ 1·12-14 ይህንም ሲያደርግ አስደናቂውን ምሥጢር እያደረገ ነው፡፡ በተወለደ ጊዜ በቤተልሔም ወተትን ከድንግልና አምላክነትን ከሰውነት፣ ሕቱም ማሕፀን ከእናትነት ጋር አንድ አድርጎ አሳይቷናል፡፡ በአምላክነት ሥራ ካልሆነ በስተቀር ወተትና ድንግልና፣ እናትነትና አገልጋይነት፣ አምላክነት እና ሰውነት፣ በአንድነት ሊገኙ አይችሉምና እግዚአብሔርን አመስግኑት ሥራህ ግሩም ድንቅ ነው በሉት እንላለን፡፡ መዝ 65·3 በሥጋዊ ጥበብ ተራቀው ሥጋዊውን ዓለም ያወቁ የአግዚአብሔርንም ሕልውና በእምነት ሳይሆን በጥበባቸው እናውቃለን ለሚሉ ሁሉ ከሰብአ ሰገል ተምረው በእምነት ሊያውቁት ይገባል፤ የተወለደው ለእነሱም ነውና፡፡
ሆኖም ግን መምጣቱን በተስፋ ለሚጠባበቁ የልደቱን ነገር በፍጹም እምነት ለተቀበሉ ሁሉ እነሆ ያማረ የምሥራች በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩት ሁሉ የሕይወት ብርሃን ተወልዷልና ደስ ይበላችሁ፡፡ በብርሃኑ ጨለማ ተወግዷልና እግዚአብሔር በይሁዳ ታወቀ፡፡ ስሙም በእስራኤል ታላቅ ነው ተብሎ እንደተነገረ የእስራኤል ንጉሥ በእስራኤል ልጅ አድሮ የዳዊት አምላክ ከዳዊት ልጅ ሥጋን ተዋሕዶ ከቀድሞ ጀምሮ ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ተልከው መንፈስ ቅዱስ እንዳናገራቸው ዓለምን ለማዳን ከጽዮን የሚወጣ ከያዕቆብ በደልን የሚያርቅ ጌታ ይወርዳል፤ ይወለዳል በማለት በየወገናቸው በየዘመናቸው የተናገሩት ትንቢት እነሆ ዛሬ ተፈጸመ፡፡ እሱም እናንተን ከመውደዴ የተነሣ ሰው ለመሆን ወደናንተ መጣሁ፡፡ በሕፃንም መጠን ተወለድኩ፤ በጨርቅም ተጠቀለልኩ፤ ፍቅሬንም ገለጥኩላችሁ ብሏልና፣ እርስ በርሳችሁ የምትፋቀሩ የወንጌል ልጆች ወንድሞች ሆይ ይህን ትሕትናና ፍቅር አይተን እርስ በርሳችን እንፋቀር፡፡ ዮም ተወልደ ፍቅር ወሰላም ዮም ተወልደ ቤዛ ኵሉ ዓለም እግዚእ ወመድኅን ዮም ተወልደ ከሣቴ ብርሃን እያልንም እንዘምር፡፡

- ስብሐት ለእግዚአብሔር አብ
- ልጁን ውረድ ተወለድ ብሎ ለሰደደው ለአብ ወላዲ አሥራፂ ተብሎ መመስገን ይገባዋል፡፡
- ለወልድም ተወለደ ተብሎ መመስገን ይገባዋል፡፡
- ማሕየዊ ለሚሆን ለመንፈስ ቅዱስም ሠራፂ ተብሎ መመስገን ይገባዋል
- ሥጋን ላጸናው ለአብ ለተዋሓደ ለወልድ ላዋሓደ ለመንፈስ ቅዱስ ዛሬም ዘወትር በእውነት ምሥጋና ይገባዋል፡፡
- ለዓለሙ ሁሉ ሕይወትን ለወለደች ለድንግል ማርያም ምስጋና ይገባል፤ የድኅነታችን መመኪያ ናትና

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 ከደቀ መዝሙር አባ ሳሙኤል ንጉሤ ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም አዳሪ ት/ቤት የሊቅ ተማሪ

መንክር ስብሐተ ልደቱ፤ የመወለዱ ምሥጢር ድንቅ ነው መንክር ስብሐተ ልደቱ፤ የመወለዱ ምሥጢር ድንቅ ነው

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/2058-2016-01-06-ledet