በዓለ ደብረ ታቦር

  • ‹‹ተፈሥሑ በእግዚአብሔር ዘረድአነ፤
  • ወየብቡ ለአምላከ ያዕቆብ፤
  • ንሥኡ መዝሙረ ወሀቡ ከበሮ፤
  • መዝሙር ሐዋዝ ዘምስለ መሰንቆ፤
  • ንፍሑ ቀርነ በዕለተ ሰርቅ፤
  • በእምርት ዕለት በዐልነ፤
  • እስመ ሥርዓቱ፤ ለእስራኤል ውእቱ››

በዓለ ደብረ ታቦር በረዳታችን፣ በረድኤታችን በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ለያዕቆብም አምላክ እልል በሉ፤ ዝማሬውን አንሡ፤ ከበሮውንም ስጡ ደስ የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆው ጋር በመባቻ ቀን በከፍተኛው በዐላችን ዕለት፣ መለከትን ንፉ፤ የቤተ እስራኤል ሥርዓት ነውና› ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት (መዝ. 80፡1-4)

በዚህ መዝሙረ ዳዊት መነሻነት ከዚህ በላይ በተነገረው መዝሙረ ዳዊት መሠረት ይህን በዐለ ደብረ ታቦር በዐላችንን በየገዳማቱና አድባራቱ በየገጠሩ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በታላቅ ሥነ ሥርዓት እናከብረዋለን፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ በዓባይ ሸለቆ ዙሪያ፣ በቀይ ባሕር አካባቢ የምትገኝ በመጽሐፍ ቅዱስና በዓለም አቀፍ ታሪክ የታወቀች ቢሆንም በበለጠ የታቀወቀችውና የምትታወቀው ስመ እግዚአብሔርን በመጥራት፤ ስሙን በመቀደስ፤ ቃሉን በመስማት በምትፈጽመው አምልኮተ እግዚአብሔር ነው ፡፡

‹‹በዕውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ ዕውነት ነውና›› ይላል የእግዚአብሔር ቃል (ዮሐ. 17፡17)

የበዐላት አክብሮት ስነ ሥርዓት፣ ዓለም ከተፈጠረ፣ ዘመን ከተቈጠረ ጀምሮ በዘመነ አበው ባልተጻፈ ሕግ፣ በሕገ ልቡና እስከሙሴ ደብረ ሲና በይቀጥላልም ከሙሴ ደብረ ሲና እስከ ዘመነ ሥጋዌ ልደተ ክርስቶስ፣ በዘመነ መሳፍንት፣ በዘመነ ነገሥት፣ በዘመነ ካህናት በሕገ ኦሪት፤ ከጊዜ በኋላም ዘመነ ሥጋዌ ልደተ ክርስቶስ መነሻ ሁኖ እስከዛሬ፣ ከዛሬም እስከ ዓለም ፍጻሜ በሕገ ወንጌል ቅዱሳት በዐላት ሲከበሩ ቆይተዋል፤ አሁንም በመከበር ላይ ናቸው፤ በዚሁ ዓይነት የበዐላቱ አከባበር እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚዘልቅ ይሆናል፡፡

ቃለ እግዚአብሔር ወልድ በገሊላ አውራጃ በናዝሬት ከተማ ሰው ሁኖ በይሁዳ አውራጃ በዳዊት ከተማ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ ተወልዶ ሰው በሆነበት በገሊላ አውራጃ በናዝሬት ከተማ አድጎ በሠላሳ ዘመኑ በይሁዳ አውራጃ በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ተጠምቆ ሳይውል ሳያድር ወደገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ዓርባ መዓልት፤ ዓርባ ሌሊት ጾሞ፣ ጸልዮ ተፈትኖ ፈተናውን ድል አድርጎ ሱባኤውን ፈጽሞ በወጣ በሦስተኛው ቀን በገሊላ አውራጃ በቃና መንደር እናቱ ቅድስት ማርያምንና ቅዱሳን ሐዋርያቱን በማስከተል በዶኪማስ ሠርግ ቤት ተገኝቶ ውሀውን ወደ ወይንነት በመለወጥ የመጀመሪያውን ተአምር በማድረግ ትምህርቱን ተአምራቱን በማድረግ ሥራውን ቀጠለ፤ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራውን የጀመረው በጥምቀት፣ በጾም፣ በጸሎት ነው ፡፡

እንግዲህ ዘመነ ሥጋዌ ልደተ ክርስቶስ መነሻ ሁኖ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በይሁዳ፣ በሰማርያና በገሊላ አውራጃዎች እየተዘዋወረ ያስተምር በነበረበት ጊዜ ነሐሴ 13 ቀን በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት ዕለት ነው ፡፡ (ማቴ 17፡1-9)

ይህ ታላቅ በዐል በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በቅዳሴ፣ በውዳሴ፣ በዝማሬ በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ በታላቅ ስነ ሥርዓት ይከበራል ፡፡ ዛሬም በዚያው ዓይነት አክብሮቱ ቀጥሏል፡፡

‹‹ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ፤ ወይሴብሑ ለስምከ፤ መዝራዕትከ ምስለ ኃይል›› ‹ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል፤ ስምህንም ያመሰግናሉ፤ ክንድህ ከኃይልህ ጋር ነው› ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት (መዝ. 88፡12-13)

ይህም ትንቢቱ እንደተነገረ የተፈጸመበት ቦታ ይኸው ደብረታቦር ነው፤ ታቦርና አርሞንኤም ማዶ ለማዶ የሚተያዩ ናቸው ፡፡

ታቦር የሚለው ስያሜ በመጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ 19 ቁጥር 34 ላይ ይገኛል ፡፡ ታቦር የይሳኮርና የዛብሎን ድንበር የነበረ መሆኑ ይነገራል፡፡ በይቀጥላልም ነቢያቱ ዲቦራና ባርቅ እስራኤልን ከምድያም ሕዝብ ቀንበር ነፃ ለማውጣት ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት በማለት ደብረታቦርን የሠራዊት መከማቻ የጠላት መመከቻ አድርገውት ነበር፤ መሳፍንት ምዕራፍ ዐራትን መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ እነዚህ ሁለት ነቢያት ዲቦራና ባርቅ ለእስራኤል የደኅንነትና የነፃነት ሥራ የሠሩበት ተራራ ነው፤ ተራራነቱም በምድረ ከነአን ካሉት ተራራዎች ሁሉ እንደሚበልጥ፣ እንደሚያምር፣ እንደሚረዝምም ለማየትና ለመመልከትም የሚያስፈራ ግሩምና ድንቅ እንደሆነ ነቢዩ ኤርምያስ አመልክቷል፡፡

በምድረ ግብፅ የሚመጣውን መቅሰፍት ሲያሳውቅ ናቡከደነፆር በትዕቢቱና በግርማ መንግሥቱ ብዙ ሠራዊት አሠልፎ ወደ ግብፅ መዝመቱን ሲያስረዳና ሁኔታውንም ሲያመለክት እንደታቦርና በባሕር ዳር እንደሚገኘው እንደቀርሜሎስ ተራራ መስሎ መጣ ይላል (ኤርምያስ 46፡18)

‹ታቦርና አርሞንኤም በስምህ አምነው በተደረገላቸው ተአምር ደስ ይላቸዋል፤ ስምህን ያመሰግናሉ፤ ለስምህም ምስጋናን ያቀርባሉ› በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ይዘምራል ፡፡ (መዝ. 88፡12)

የእስራኤላውያን የእምነት ትምህርት የተመሠረተው በብሉይ ኪዳኑ በተገለፀው በአንድ አምላክ ማመን ሲሆን በማንኛውም በኩል ሕይወታቸውን የሚገዛና የሚመራ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ደኅና አድርገው በመማራቸውና በማወቃቸው በሕይወታቸው ሁሉ ተቀዳሚ ተግባር የሚያደርጉት የእምነታቸውን ሕግና ስነ ሥርዓት መፈጸም በመሆኑ እስራኤላውያን ከሳምንቱ በዐላቸው ከሳባት (ከቅዳሚት) ሌላ ሌሎች ዓመታውያን በዐላት ያሏቸው መሆኑን የሙሴ መጻሕፍት ይነግሩናል ፡፡

ከዚህም ጋር ከክርስትናው ታሪክ አመሠራረት ጀምሮ በየጊዜው የነበሩትና ያሉት ሁሉ የአምልኮታቸው የሕግ አቋምና ሥርዓት በሚፈቅደው መሠረት አምላካቸውን የሚቀድሱበት፣ የሚያወድሱበት፣ ለአምላካቸው መሥዋዕት የሚያቀርቡበት ጥንታውያን ዓለም አቀፍ የሆኑ የተከበሩ፣ የሚከበሩ በዐላት የነበሯቸው፣ ያሏቸው የሚኖራቸው መሆኑን የሃይማኖት ታሪክ ሒደት ያስተምራል ፡፡

ከዚህ አንፃር ይህ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በውዳሴ፣ በቅዳሴ በታላቅ ስነ ሥርዓት የምናከብረው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዓበይት በዐላት በዐራተኛ ደረጃ ያለ አንዱ ዓቢይ በዐል ነው ፡፡

እነዚህም ዘጠኝ ዓበይት የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዐላት፤

1ኛ. ጽንሰቱ ወይንም ብስራቱ፤ መጋቢት 29 ቀን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሁኖ ከእርሷ እንደሚወለድ ቅድስት ድንግል ማርያምን ያበሰረበት ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ሰው የሆነበት ዕለት ነው፤ ‹‹ቃል ሥጋ ኮነ ወኀደረ ላእሌነ››

2ኛ. ልደቱ፤ ታኅሣሥ 29 ቀን በትንቢተ ነቢያት የተነገረለት ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሁኖ ሰውን ለማዳን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በዳዊት ከተማ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ የተወለደበት ዕለት ነው፤

3ኛ. ጥምቀቱ፤ ጥር 11 ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም፤ አርአያ፣ ምሳሌ ለመሆን፣ ውሀውን ለመቀደስ፣ ለጥምቀት ኃይልን ለመስጠት በተወለደ በሠላሳ ዓመቱ በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ወልደ ዘካርያስ የተጠመቀበት ዕለት ነው፤

4ኛ. ደብረ ታቦር፤ ነሐሴ 13 ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በይሁዳ፣ በሰማርያ በገሊላ አውራጃዎች እየተዘዋወረ ያስተምር በነበረበት ጊዜ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኰቱን፣ ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት ዕለት ነው፤

5ኛ. ሆሣዕና፤ ከትንሣኤ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በሚውለው እሑድ የሚከበር ነው፤ ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያይቱና በአህያይቱ ውርጫ ሁኖ እየተመሰገነ ወደቤተ መቅደስ የገባበት ዕለት ነው፤

6ኛ. በዐለ ስቅለት፤ ከትንሣኤ በፊት በዋለው፣ በሚውለው ዓርብ መድኃኔ ዓለም፣ የዓለም ቤዛ ለመሆን በማዕከለ ምድር ቀራንዮ ጎልጎታ ኢየሩሳሌም የተሰቀለበት ዕለት ነው፤

7ኛ. ትንሣኤ ዕለተ እሑድ፤ በዐለ ትንሣኤ፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን በማዕከለ ምድር ቀራንዮ ጎልጎታ ኢየሩሳሌም ተሰቅሎ በሥጋ ሞቶ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ውሎና አድሮ መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ከሙታን ተለይቶ የተነሣበት ዕለት ነው፤

8ኛ. ዕርገት፣ ዕለተ ሐሙስ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በዓርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ያረገበት ዕለት ነው፤

9ኛ. ጰራቅሊጦስ፣ ዕለተ ዕሑድ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በሐምሳኛው፣ ባረገ በዐሥረኛው ቀን ቀደም ሲል ከማረጉ በፊት ‹‹አንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እምአርያም›› ‹ከላይ ከአርያም ኃይልን እስከምትጎናጸፉ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ› በማለት ለሐዋርያቱ በነገራቸው የተስፋ ቃል መሠረት መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደበት ዕለት ነው ፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዓበይት በዐላትና አመጣጣቸው ከዚህ በላይ እንደታየው ነው ፡፡

ከእነዚህ ከዘጠኙ መካከል ሆሣዕና፣ ስቅለት፣ ትንሣኤ፣ ዕርገትና ጰራቅሊጦስ በዐላት፣ ዐዋድያት ስለሆኑ በቀን አቈጣጠር መባቻ ሐመርን ተከትለው ወደላይና ወደታች ይላሉ፤ ይሁንና ዕለታቸው አይፋለስም፤ ሆሣዕና፣ ትንሣኤ፣ ጴራቅሊጦስ፣ እሑድን፣ ስቅለት ዓርብን፣ ዕረገት ሐሙስን አይለቅም፤ ሌሎቹም ማለት ፅንሰቱ፣ ልደቱ ጥምቀቱ፣ ደብረ ታቦር ግን ዐዋድያት አይደሉም፤ ይሁንና ዕለታቸው የተፋለሰ ነው ፡፡

ይህ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በዛሬው ዕለት በታላቅ ስነ ሥርዓት የምናከብረው በዐላችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድስት ሀገር ኢየሩዳሌም እየተዘዋወረ በማስተማር በነበረበት ጊዜ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኰቱን፣ ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት ዕለት ነው ብለናል፤ ታቦር ከገሊላ ባሕር በደቡብ ምዕራብ የሚገኝ በዘመነ መሳፍንት ታሪክ የተሠራበት መጠነኛ ተራራ ነውም ብለናል ፡፡

ስለ ደብረ ታቦር በሕግና በነቢያት የተነገሩ ትንቢቶችና የተገለጡ ምሳሌዎች መኖራቸውን ቀደም ሲል ሰምተናል ፡፡

አርሞንኤም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደደብረ ታቦር ከመውጣቱ በፊት እንደ ቅዱስ ማቴዎስና እንደ ቅዱስ ማርቆስ አጻጻፍ ከስድስት ቀናት በፊት፣ እንደቅዱስ ሉቃስ አጻጻፍ ከስምንት ቀናት በፊት በቂሣር ዘፊልጶስ ሁኖ ‹‹መነ ይብልዎ ስብእ ለወልደ እጓለ እመሕያው›› ‹ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል› የሚለውን ጥያቄ ለሐዋርያቱ ባቀረበበት ቦታ አካባቢ የሚገኝ ከደብረ ታቦር የራቀ ሁኖ ለደብረ ታቦር በዕይታ አንፃር የቀረበ ነው ፡፡

በሐዲስ ኪዳን ሦስቱ ወንጌላውያን ቅዱስ ማቴዎስ፣ ቅዱስ ማርቆስና ቅዱስ ሉቃስ የተራራውን ስም ሳይጠሩ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ ሐዋርያት ከቅዱስ ጴጥሮስ፣ ከቅዱስ ያዕቆብና ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር በመሆን ወደረጅም ተራራ እንደወጣና በዚያም በተራራው ላይ መልኩና ልብሱ እንደተለወጠ በሰው ዓይን ሊታይ የማይችል ብርሃን እንደለበሰና ሦስቱ ሐዋርያትም የብርሃኑን ግርማ ማየት ተስኗቸው በምድር ላይ እንደወደቁ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሁለቱ ነቢያት መገብተ እስራኤል ከነበሩት ከሙሴና ከኤልያስ ጋር እየተነጋገረ ሳለ ‹‹ይህ ነው የምወደው ልጄ በእርሱም ደስ የሚለኝ እርሱን ስሙት›› የሚል ድምፅ እንደሰሙ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላነቱን ግርማ እንደገለጠ የአብ ልጅነቱንም እንዳስመሰከረ ሦስቱ ወንጌላውያን ነግረውናል፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፤ ይህኑ አንሥቶ በተቀደሰው ተራራ ላይ የመጣለትን ሰማያዊ ቃል እንደሰማነው እኛ ምስክሮች ነን ብሎ ጽፏል (2ኛ ጴጥሮስ 1፡18)

ደብረ ታቦር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደደብረ ታቦር ወጥቶ ክብሩን የገለጠበት አምላክነቱን ያሳወቀበት ከፍተኛ ክብር የተሰጠው ተራራ ነው፤ በዚህም ምክንያት ነው የከበረ ታሪካዊ ተራራ ነው የምንለው፡፡

ታቦር የሚለው ስያሜ በመጽሐፈ ኢያሱ በምዕራፍ 19 በቁጥር 11-14 ላይ ይገኛል፤ ታቦር የይሳኮርና የዛብሎን ርስት አካፋይና አዋሳኝ ድንበር የነበረ መሆኑን ያመለክታል፤ በመቀጠልም በመጽሐፈ መሳፍንት ዲቦራና ባርቅ እስራኤላውያንን ከምድያም ሕዝብ ቀንበር ነፃ ለማውጣት ክተት ሠራዊት፣ ምታ ነጋሪት፤ ብለው ደብረ ታቦርን የሠራዊት መከማቻ የጠላት መመከቻ አድርገውት ነበር (መሳ. 4) ደብረ ታቦር እነዚህ ሁለቱ ዲቦራና ባርቅ ለእስራኤላውያን የደኅንነታቸውንና የነፃነታቸውን ተግባር የፈጸሙበት ተራራ ነው፤ ተራራነቱም በምድረ ከነዐን ካሉት ተራሮች ሁሉ እንደሚበልጥ እንደሚያምርና እንደሚረዝም ለማየትም የሚያስፈራ ግሩም፣ ድንቅ እንደሆነ ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ አመልክቷል ፡፡ በምድረ ግብፅም የሚመጣውን መቅሰፍት ነቢዩ ኤርምያስ ሲያሳውቅ ናቡከደነፆር በግርማ መንግሥቱ ከብዙ ሠራዊቱ ጋር ተሠልፎ ወደግብፅ መዝመቱን ሲያስረዳና ሁኔታውን ሲያመለክት ‹‹እንደታቦርና በባሕርዳር እንዳለው እንደቀርሜሎስ ሁኖ ወይንም መስሎ መጣ›› በማለት ለምሳሌው ታቦርንና ቀርሜሎስን ጠቅሷቸዋል፡፡ (ኤር. 46፡18-28)

በሐዲስ ኪዳንም ሦስቱ ወንጌላውያን ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ እንደጻፉት የተራራውን ስም ሳይጠሩ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ሐዋርያት ማለት ቅዱስ ጴጥሮስን፣ ቅዱስ ያዕቆብንና ቅዱስ ዮሐንስን አስከትሎ ሊጸልይ ወደረጅም ተራራ እንደወጣ በዚያም መልኩና ፊቱ እንደተለወጠ፣ በሰው ዓይን ሊታይ የማይችል ብርሃንን እንደለበሰ፣ ጌታችን መድኃኒችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለቱ ነቢያተ እግዚአብሔር ከሙሴና ከኤልያስ ጋር ወደፊት በኢየሩሳሌም በማዕከለ ምድር ቀራንዮ ስለሚቀበለው ሕማማተ መስቀል እንደተነጋገረ ወዲያውም ከሰማይ ‹‹በርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት›› የሚል ድምፅ እንደሰሙ ሐዋርቱም የብርሃኑን ግርማ ማየትና ከላይ የመጣውን ድምፅ መስማት ተስኗቸው በምድር ላይ እንደወደቁ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የአምላክነቱን ግርማ ማለት ግርማ መለኰቱን እንደገለጠ፤ የአብ የባህርይ ልጅነቱንም እንዳስመሰከረ ነግረውናል፡፡

‹‹ንግበር ሠለስተ ማኅደረ፣ አሐደ ለከ፣ ወአሐደ ለሙሴ፤ ወአሐደ ለኤልያስ›› በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሦስት ሰቀላዎችን ሠርተው በደብረ ታቦር መኖር ለእነርሱ መልካም መሆኑንም አሳስቦ ነበር ፡፡

ይህም፣ አምላክ ሰው የሆነበትን አላማ ትቶ በደብረ ታቦር ሰቀላ-ቤት ሠርቶ ራሱን በተራራ ላይ ሰውሮ ይኖር ዘንድ ቅዱስ ጴጥሮስ ደፍሮ መናገሩ ፍጹም አለመሆኑን የሚያመለክት ነው፤ ይሁንና በዚያን ጊዜ ሐዋርያት ፍጹማን ባለመሆናቸው የዕውቀት ማነስ ይታይባቸው ነበርና ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሰው እጅ በተሠራ ቤት መኖር የማይፈልግ ለመሆኑ በተራራው የነበሩትን ሐዋርት በደመና መጋረዱ ነው፡፡

እግዚአብሔር በነቢዩ ኢሳይያስ አንደበት የተናገረው፤ ወይንም ያናገረው ‹‹ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ ማረፊያ ዱካ ናት፤ ታዲያ ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠሩልኛላችሁ? የማርፍበትስ ቦታ ምን ዓይነት ነው? ዓለምን የፈጠርሁ እኔ ራሴ ነኝ፤ ነገር ግን እኔ ደስ የምሰኘው ንስሐ ገብተው በሚታዘዙኝና በሚፈሩኝ ትሁታን ነው›› ይላል ፡፡ (ኢሳይያስ 66፡1-3)

በሌላም ዘይቤ ቅዱስ ጴጥሮስ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለሙሴ፣ ለኤልያስ ሦስት ሰቀላዎች እንሥራ ብሎ ማሰቡ ትሁትነቱን የሚያመለክት ነው ፡፡

በዚህም ተራራ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነቱን፣ የባህርይ ልጅነቱን ከአብ አስመስክሮበታል፤ ምሥጢረ ሥጋዌ ከሦስቱ አካላት ሁለተኛው አካል ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም በዳዊት ከተማ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ በሥጋ የመገለጡ አምላክ ሰው፣ ሰው አምላክ የመሆኑ ምሥጢር ነው፤ ‹‹ቃል ሥጋ ኮነ፤ ወኀደረ ላዕሌነ›› ‹ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ› ይላል ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ (ዮሐ. 1፡14)

ስለዚህ በምሥጢረ ሥጋዊ የሚገለጠው ትምህርት፣ ክርስቶስን ቃለ አብ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ድንግል ማርያምን በአማን ወላዲተ አምላክ ብሎ ማመን ነው ፡፡ (ቄርሎስ ሃይ.አ)

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ይህኑ መነሻ በማድረግ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ገንዘብ አድርጓልና ይህንም ቃል እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን›› ብሏል ፡፡ (2ኛ ጴጥ. 1፡17-19)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ ሐዋርያት ጋር ወደደብረ ታቦር ወጥቶ ክብሩን የገለጠበት፤ አምላክነቱን ያሳወቀበት ብርሃነ መለኮቱ የታየበት ክብር የተሰጠው ተራራ ነውና በዚህ ምክንያት በእግዚአብሔር ስም በዛሬው ዕለት በዐለ ደብረ ታቦር በታላቅ ስነ ሥርዓት ይከበራል ፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም ‹‹ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዜአከ ይትፌሥሑ፤ ወይሴብሑ ለስምከ›› ‹ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል ስምህንም ያመሰግናሉ› በማለት ተናግሮታል ብለናል፡፡

ይህም ትንቢቱ እንደተነገረ ትንቢቱ የተፈጸመበት ቦታ ይኸው ደብረ ታቦር ነው፤ ታቦርንና አርሞንኤምን ማዶ ለማዶ ማየት ይቻላል፤ ታቦርና አርሞንኤምም በርቀት ይታያሉ፤ ይተያያሉ፡፡ እግዚአብሔር በነቢያቱ አንደበት ከተናገረውና ካናገረው አንድም የቀረ ትንቢት የለም፤ ተነግሮ ያልተፈጸመ ትንቢት ቢኖር የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ብቻ ነው፤ ‹‹ድልዋኒክሙ ነበሩ እስመ ኢተአምሩ ጊዜ ይመጽእ ሐዳስ በዐለቤት እመሂ ሰርከ፣ ወእመሂ መንፈቀ ሌሊት፣ ወእመሂ ጎሀ ጽባህ፣ ድልዋኒክሙ ነበሩ›› ‹ጌታ በሠርክ፣ በዕኩለ ሌሊት፤ በማለዳ እንደሚመጣ አይታወቅምና ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ› ይላል የእግዚአብሔር ቃል (ማቴ. 24፡44) ስለዚህ ተዘጋጅተን በመጠባበቅ ላይ መገኘት ይኖርብናል ፡፡

ደብረ ታቦር እንደሌሎቹ ቅዱሳት መካናት ሁሉ በታላቁ እስጠንጢኖስ ዘመነ መንግሥት ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶበት የፋርሳውያን ዘመን፣ ዘመቻ ጊዜ፣ አይሁድ ክርስቲያኖችን የጎዱና ፋርሳውያንን የረዱ መስሏቸው፤ በገሊላ አውራጃ ተሠርተው የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ሲሠሩ፣ ሲፈርሱ ነበር፤ ይልቁንም በተንባላት (በእስላሞች) ዘመን በደብረ ታቦር የነበረውን ቤተ ክርስቲያን አፍርሰው ምሽግ ሠርተውበት የነበረ መሆኑ ይነገራል ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በደብረ ታቦር ግሪኮችና ላቲኖች የየራሳቸው የሆኑ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት አሏቸው ፡፡ ግሪኮች ከተሠራ የቆየ ቤተ ክርስቲያን ያላቸው ሲሆን፤ ላቲኖችም በቀድሞ የቤተ ክርስቲያን ፍራሽ ቦታ አዲስ የተሠራ ቤተ ክርስቲያን አላቸው፤ ይህ ቤተ ክርስቲያን በውስጡ ስድስት መቅደሶች ያሉት ሦስቱ፣ ጌታን ተከትለው በወጡት በሦስቱ ሐዋርያት ስም ሲሆን፣ ሁለቱ መቅደሶች ደግሞ በሁለቱ ነቢያት ማለት በሙሴና በኤልያስ ስም ነው፤ አንዱና ዓይነተኛው መቅደስም፤ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሚጠራ ነው ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎቹን ሐዋርያት በእግረ ደብር ትቶ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ተራራው መውጣቱና በዚያም ተራራ የሆነውን ተአምር እነዚህ ሦስት ሐዋርያት በማየታቸው ለሐዋርያዊነት ሥራቸውና ለእምነታቸው ጽናት ትምህርትን የሰጣቸው መሆኑን እንረዳለን ፡፡

ከእነዚህም ሦስት ደቀመዛሙርት አንዱ የአይሁድና የአማልክት አምላኪዎች ሐዋርያ የነበረው ቅዱስ ጴጥሮስ ነው፤ ቅዱስ ዮሐንስም የአሕዛብ ሐዋርያ የነበረ በራእዩ ምዕራፍ ሁለትንና ሦስትን ለጻፈላት በመካከለኛው ምሥራቅ በኤፌሶን ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያ የነበረ ነው ፡፡

ቅዱስ ያዕቆብ በማዕከለ ምድር ኢየሩሳሌም ስለ ክርስቶስ ሲመሰክር የተገደለ ከሐዋርያት መካከል የመጀመሪያው ሰማዕት ነው፡፡ በደብረ ታቦር ለሦስቱ ሐዋርያት የተገለጠው ምሥጢር በእግረ ደብር የቀሩትም ሐዋርያት በዚያው እንዳሉ በተአምር ምሥጢሩን ያዩ መሆኑ የሚነገር ቢሆንም ፈቃደ እግዚአብሔር ሁኖ ወጥተው ዐይተውት ቢሆን ኖሮ ለሐዋርያነት ሥራቸው የበለጠ ኃይልን ይሰጣቸው ነበር፤ ይህ ዓይነቱ ተአምራታዊ ዕይታ ኃይል ይሆናልና ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ ሐዋርያት ጋር ወደደብረ ታቦር በወጣ ጊዜ ሙሴ የሕዝበ እግዚአብሔር ቤተ እስራኤል መሪ የነበረ፣ በናባው ተራራ ሞቶ የተቀበረ፣ መቃብሩ የማይታወቅ ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተው በእግዚአብሔር መንግሥት ያሉትን ሁሉ ወክሎ ተገለጠ፤ (ማቴ. 13፡43፣ ሉቃስ 9፡30-31) ነቢዩ ኤልያስም ሳይሞቱ የተሰወሩትን፣ የሚሰውሩትን የሚለወጡትን በመወከል በደብረ ታቦር የተገለጠ ነው፡፡ (1ኛ. ቆሮ. 15፡ 50-57፣ 1ኛ ተሰ. 4፡14-17)

ቅዱስ ጴጥሮስ በቂሣርያ ዘፊልጶስ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ስለመሰከረ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ ለመቀበል ተስፋውን ካገኘ በኋላ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገና የመከራውንና የሞቱን ነገር በመናገሩ ቅዱስ ጴጥሮስና ሌሎቹም ቅዱሳን ሐዋርያት እጅግ በጣም አዝነውና ተክዘው ነበርና ጌትነቱንና ክብሩን አሳይቶ ኀዘናቸውን ወደደስታ ለመመለስ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስና ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ በየወንጌላቸው እንደጻፉት በስድስተኛው ቀን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ሦስቱን ሐዋርያት ብቻ ይዞ በገሊላ አውራጃ ከናዝሬት ከተማ ወደ ምሥራቅ በኩል ወደአለው ረጅም ተራራ ወጣ፤ ወንጌላዊው ሉቃስም በስምንተኛው ቀን ይላል ይህን ተራራ ሦስቱ ወንጌላውያን ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ ረጅም ተራራ ከማለት በቀር ስሙን አልጠሩትም ብለናል ፡፡

ይሁንና ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ይህን የተራራውን የደብረ ታቦር ታሪክ ፈጽሞ አልነካውም፤ በመጽሐፈ መሳፍንትና በመዝሙረ ዳዊት ብቻ ታቦር ተብሎ ስሙ ተጠርቷል ብለናል ፡፡ (መሳ. 4፡6-15፣ መዝ. 88፡12) በሌሎች የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትም ታቦር ተብሎ ተጽፎ ይገኛል፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙን ሐዋርያት በእግረ ደብር ትቶ ሦስቱን ማለት ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ብቻ ይዞ ወደተራራው ጫፍ በደረሰ ጊዜ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፊቱ እንደፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደበረዶ ነጭ ሆነ ብለናል፡፡

ሙሴና ኤልያስም መጥተው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩ፤ ሙሴና ኤልያስ በደብረ ታቦር ከጌታችን ጋር መታየታቸው ለቅዱስ ጴጥሮስና ለሌሎቹም ሐዋርያት እምነታቸውን የሚያረጋግጥላቸውና የሚያጸናላቸው መሆኑ አያጠራጥርም ብለናል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት ከስድስት ወይንም ከስምንት ቀናት በፊት በጎላን ተራራ ሰሜናዊ አቅጣጫ በአርሞንኤም ተራራ አካባቢ በቄሣርያ ዘፊለጶስ ሳሉ ‹‹መነ ይብልዎ ሰብእ ለወልደ እጓለመ ሕያው›› ‹ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል› ብሎ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርቱን በጠየቃቸው ጊዜ ‹‹መጥምቁ ዮሐንስ፣ ኤልያስ፣ ኤርምያስ ወይንም ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ሙሴ ነው ይሉሃል›› ብለው ነበርና፤ አሁን ግን ሙሴና ኤልያስ መጥተው በደብረ ታቦር ከጌታ ጋር ሲነጋገሩ በመታየታቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሴ ወይንም ኤልያስ አለመሆኑ በግልጥ ታወቀ ማለት ነው፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም የሁሉም ቅዱሳን ሐዋርያት አፈጉባኤ ሁኖ በቂሣርያ ዘፊልጶስ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን መስክሮ ነበርና በደብረ ታቦር አምላክነቱን ጌትነቱን ሲገልጥ እጅግ በጣም ደስ ስለአለው ቅዱስ ጴጥሮስ በደብረ ታቦር ወደጌታችን ቀርቦ ‹‹ንግበር ሠለስተ ማኅደረ፤ አሐደ ለከ፤ ወአሐደ ለሙሴ ወአሐደ ለኤልያስ›› ‹ሦስት ሰቀላዎችን እንሥራ፣ እነዚህም ሰቀላዎች አንዱ ለአንተ፣ አንዱ ለሙሴ፣ አንዱም ለኤልያስ ይሆናሉ›› አለው ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ በደብረ ታቦር ለመኖር አስቦ ሦስት ሰቀላዎችን ብቻ እንሥራ ብሎ በተናገረ ጊዜ አንዱን ለአንተ አንዱን ለሙሴ፣ አንዱንም ለኤልያስ አለ እንጂ፣ ለእኔና ለጓደኞቼ ሐዋርያት በማለት አልተናገረም፤ ይህም የቅዱስ ጴጥሮስ ዘይቤ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ቤተ ሰብእ ሁኖ ጌታውን ፈጣሪውን እያገለገለ ከጌታው ከፈጣሪው ጋር አብሮ ለመኖር ማሰቡን የሚያስረዳ እንጂ ከጌታው ከፈጣሪው ተለይቶ ለብቻው ጌታ፣ ሐዋርያ ሆኖ መኖር አለመፈለጉን የሚያመለክት፤ የሚያሰረዳ ነው ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ስለቤቱ አሠራር እየተናገረ እያለ በድንገት ብሩህ ደመና መጥቶ ሰወራቸው፤ ከደመናውም ‹‹የምወደው፤ በእርሱም ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት›› የሚል ድምፅ መጣ፤ ደቀ መዛሙርቱም ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ከድንጋጤና ከፍርሃት የተነሣ በግባራቸው ወደቁ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አይዟችሁ፤ አትፍሩ ብሎ ከወደቁበት አነሣቸው፤ ከተነሡም በኋላ ዓይናቸውን አቅንተው ቢመለከቱ ሙሴና ኤልያስ ወደመጡበት ስለተመለሱ ከጌታችን በቀር ማንንም አላዩም (ማቴ. 17፡1-10)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቂሣርያ ዘፊልጶስ ‹‹መነ ይብልዎ ሰብእ ለወልደ እጓለ ሕያው›› ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል›› ብሎ ሐዋርያቱን በጠየቃቸው ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ የሁሉም ሐዋርያት አፈ ጉባኤ ሁኖ ‹‹አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው›› ‹አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ› በማለት መስክሮ በዚሁም ‹‹ብፁዕ›› ተብሎ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ ቁልፍ እንደሚቀበል ተስፋውን ተቀብሎ ነበርና በዚያን ጊዜ በደብረታቦር እግዚአብሔር በደመና ውስጥ ሁኖ ‹‹የምወደውና በእርሱም ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነውና እርሱን ስሙት›› በማለት የክርስቶስን የባህርይ ልጅነቱን ስለመሰከረ የቅዱስ ጴጥሮስ የቂሣርያ ዘፊልጶስ ምስክርነቱን አደላድሎ መናገሩን ያስረዳናል፤ ይህም ለቅዱስ ጴጥሮስ በአጠቃላይ ለቅዱሳን ሐዋርያቱ ታላቅ ደስታና ክብር ሆናቸው ብለናል ፡፡

ይሁንና ቅዱስ ጴጥሮስ የፍጡር ሰው ምስክርነት ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔር እንደዚህ ብሎ በመናገሩ ደስታው ከፍ ያለ ሆነ፤ ለደስታውም ወሰን አልነበረውም፡፡

እንግዲህ ከፍ ብሎ ከተነገረው ታሪክ የምንረዳው ሙሴ በደብረ ታቦር የተገኘው ኦሪቱንና የሞቱትን ሁሉ በመወከል ሲሆን፤ ኤልያስም ከሙሴ ጋር ሁኖ በደብረ ታቦር የተገኘው ሕያዋኑን ሁሉ በመወከል ነው ብለናል ፡፡

በአጠቃላይ በዚያን ጊዜ የሙሴና የኤልያስ በደብረ ታቦር መገኘት ኦሪትንና ነቢያትን ሙታኑንና ሕያዋኑን በመወከል የተገኙ ናቸው፤ ከዚህም ጋር የሙሴና የኤልያስ በዚያ በታላቁ ታሪካዊ ተራራ ደብረ ታቦር መገኘት የቅዱሳኑን አንድነት የሚያሳይ ነው፤ ሁለቱ ሙሴና ኤልያስ ከየነበሩበት መጥተው ተገናኝተውና ተዋውቀው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መነጋገራቸው ይህ ራሱ ተአምራታዊ ድርጊት ነው ፡፡
በደብረ ታቦር በክርስቶስ መለኮታዊ ክብር መገለጥ የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ግልጥ ሁኖ ተቀምጧል፤ ይህም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባህርይ ልጅነት ሲመሰክር ከሰማይ መሰማቱ ነው (ማቴ. 17፡5)

ጴጥሮስ ያዕቆብና ዮሐንስ እነዚህ ሦስቱ ሐዋርያት ከጌታቸው ከፈጣሪያቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመሆን በደብረ ታቦር ተራራ በመገኘታቸው ይህን ምሥጢረ መለኮት በማየትና በመመልከት ሊመሰክሩ በቅተዋል (2ኛ ጴጥ. 2፡17-18)

ደብረ ታቦር
ጌታ በማስተማር በነበረበት ጊዜ በደብረ ታቦር ላይ ብርሃነ መለኮቱን ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት ታሪካዊ ተራራ ነው ብለናል (ማቴ. 17፡1-9)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህን ምሥጢረ ሥላሴ ዕውን የሆነበትን በዐል በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በታላቅ ስነ ሥርዓት የምታከብረው ከላይ የተነገረውን ታሪክ መነሻ በማድረግ ነው፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ከዚህ አንፃር ክርስቲያኖች ከተለመደው አድካሚው የዘወትር ሥራቸው ተላቀውና ዐርፈው በቤተ ክርስቲያን እየተሰበሰቡ በዐላቱን ለማክበር በሰዐቱ፣ የጸሎተ ቅዳሴው ተካፋዮች ለመሆን በቤተ ክርስቲያን ካላንደር ወይንም ቀን መቍጠሪያ እንዲሁም በስንክሣር የየዕለቱን፣ የየሳምንቱን፣ የየወሩንና የየዓመቱን በዐላት ለማወቅና ለማሳወቅ ታስቦ የበዐላቱን ቀናት በቀይ ቀለም ይጽፋሉ፤ ዓበይትና ንዑሳን በዐላት በቀይና በጥቁር ቀለማት የመስቀል ምልክት ይደረግባቸው ነበር፤ ከዚያ ሲያያዝ በመጣው አሠራር መሠረትም ቤተ ክርስቲያን አሁንም ትጠቀምበታለች፡፡

ቀዳሚት ሰንበት በሕገ ኦሪቱ በሙሴ መጻሕፍት ረጅም ታሪክ ያለው በሰባተኛው ዕለት በዕለተ ቀዳሚት የሚከበረው በዐል ነው ብለናል ፡፡

ዕለተ እሑድም በክርስትናው ሕይወት ረጅም ታሪክ ያለው በሳምንቱ መጀመሪያ የሚውለው በዐል ነው፤ ከዚህም ጋር የዚህ የደብረ ታቦር በዐል አመሠራረትና አመጣጥ ረዘም ያለ የታሪክ ጉዞ ያለው ለመሆኑ ከቅዱስ ወንጌል መረዳት ችለናል፡፡

ይህ በዐል በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በልዩ ሁኔታ የሚከበር መንፈሳዊ በዐል ነውም ብለናል ፡፡

ይህ በዐል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በተለይም በምእመናኑ ዘንድ #ቡሄ$ እየተባለ ይጠራል፤ እንደዚህ የሚሉበትም የተለያየ ምክንያት አላቸው፤ ቡሄ ማለት መላጣ ገላጣ ጠጉር የሌለው ራስ ማለት ነው ይላሉ፡፡

በሀገራችን ይህ በዐል ከመድረሱ አስቀድሞ ሕፃናቱ ጅራፍ ሲገምዱና ሲያጮሁ ይሰነብታሉ፤ እናቶችም ለዚህ በዐል የሚሆን ዳቦ ለመጋገር ስንዴያቸውን ሲያጥቡ፣ ሲፈትጉ ይሰነብታሉ፤ የሠፈር ሕፃናትም ከበዐሉ ዋዜማ ጀምረው በየቤቱ እየዞሩ "ቡሄ፣ ቡሄ" እያሉ ይጨፍራሉ፤ በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ሙልሙል ዳቦ እያነሡ ይሰጣሉ፤ ሔደውም ሙልሙል ዳቧቸውን እየበሉ ሲጋረፉ ይውላሉ፡፡

የጅራፉ ጩኸት ሐዋርያት ማለት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ በደብረ ታቦር ከላይ በሰሙት ድምፅ መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን የሚያስታውስም ይመስላል ፡፡

በየሠፈሩም ችቦ ይበራል፤ ይህም በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኰት ምሳሌ ነው፤ የቡሄ ዕለት ለዘመድ አዝማድ በእያንዳንዱ ቤተሰብ በልጆቹ ልክ ሙልሙል ዳቦ ይሰጣል፤ ከዚህም ጋር የክርስትና አባትና እናት ለክርስትና ልጆቻቸው የቡሄ ሙልሙል ዳቦ ይሰጣሉ፤ በቆሎ ደበሎ ትምህርት ቤትም ደብረ ታቦር የአስተማሪዎችና የተማሪዎች በዐል ስለሆነ ተማሪዎች ቀደም ብለው ዕህሉን፣ ጌሾውን ብቅሉን ይለምናሉ፤ ሕዝቡም ባህሉን ስለሚያውቅ በገፍ ይሰጣቸዋል፤ የደብረ ታቦር ዕለት ጠላውን ጠምቀው፣ ቆሎውን ቆልተው ዳቦውን ጋግረው ሊያስቀድሱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመጡት ምእመናን ሁሉ ከቅዳሴው በኋላ ይጋብዛሉ፤ ይህም እስከአሁን ድረስ በቆሎው፤ በደበሎው ትምህርት ቤቶች የሚሠራበት ነው፡፡

ይህን በዐል ደብረታቦርን በተመለከተ ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያውያት የሚሉት ዘይቤ አላቸው ፡፡ ይህም ዘይቤ ‹‹ደብረ ታቦር ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› የሚል ነው፤ ስለዚህም አባባል ደብረታቦር ከዋለ በኋላ ክረምት ያለ መሆኑ፤ ዶሮውም ከጮኸ በኋላ ሌሊቱ ያለ ስለመሆኑ ይናገራሉ ፡፡

ከዚህ አንፃር የበዐላት አከባበር ከአምልኮተ እግዚአብሔር ጋር ተያይዞ የመጣ፣ የሚመጣ ስለሆነ የመንፈሳዊ ሕይወት አርአያነትና ምሳሌነት የሚለካበት፤ የሚመዘንበት የሕይወት መዘክርነት ትርጉም ያለው ነው ፡፡ የበዐላት አከባበር በክርስትናው ዓለም በትምህርት አቅርቦት ከፍተኛ አገልግሎትን የሰጠ ነው ፡፡ የበዐላት አመሠራረትና አመጣጥ ከሰው ሕይወት ጋር ተጣምሮ የመጣ ትርጉምና ከፍተኛ ዋጋ ያለው ስለሆነ በዚሁ መሠረት ጥቅሙንና ትርጉሙን አውቀንና ተረድተን በዐላቱን ማክበር የእምነታችን ግዴታ ይሆናል፡፡

የቀደመውና የአሁኑ ትውልድ በድካም ያቆየውን የበዐላት አከባበር ሒደት በዚያው ዓይነት አምሮና ደምቆ እንዲቀጥል ማድረጉ ተገቢ ነው ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም የበዐላት አክብሮት ታሪኳን በመመዝገብ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፉ ኃላፊነት አለባት፡፡
እንግዲህ ያለፈውንና የጊዜውን ታሪካችንን መነሻ በማድረግ ካለፈውና ከአሁኑ ታሪካችን በመማር የአሁኑንና የወደፊቱን የበዐላት አከባበር ሒደታችንን፤ መገንባት የሚቻለው በአሁኑና በሚቀጥለው ትውልድ ብርታትና ጥረት ስለሚሆን የአሁኑንና የሚቀጥለውን ትውልድ ለዚህ አላማ በትምህርተ ወንጌል ማዘጋጀቱና ብቁ ማድረጉ አማራጭ የማይገኝለት የአሁኑ ትውልድ ተቀዳሚ ተግባር መሆኑ ታውቆ በሥራው ሒደት መታየት ይኖርበታል ፡፡

በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ በቅዱሳን መላእክት ጻድቃን ሰማዕታት ተራዳኢነት የ2005 ዓ.ም. በዐለ ደብረ ታቦር ዓመታዊ በዐላችንን በማክበር ላይ እንገኛለን ፡፡
ይህን ላደረገልን እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ለዘአብጽሐነ እስከ ዛቲ ሰዓት›› በማለት ምስጋናችንን ለእግዚአብሔር አምላካችን እናቀርባለን ፡፡

 

እግዚአብሔር አምላካችን ይባርከን፣ ይቀድሰን፤

አባ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ ዶክተር፤
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት
የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ፣

 

 

Read more http://eotcssd.org/dogma-ethiopian-orthodox-tewahedo-church/60-miscellaneous/308-debretabor.html

Add comment


Security code
Refresh