በኢትዮጵያ ሥልጣኔ የመንፈሳዊ ት/ቤቶች ሚና

ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ
የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ
በመምህራን ጉባኤ ወቅት ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ

የኢትዮጵያ ሥልጣኔና ታሪክ፣ ነጻነትና ጀግንነት፣ አንድነትና መልካም ሥነ ምግባር ዋና ምንጭ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፤

በሌሎች ክፍለ ዓለማት እንዲህ ተሟልተው የማይገኙ እነዚህ አኲሪ ዕሴቶች የተፈጠሩትና ተጠብቀው የኖሩት በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን በተስፋፉ ት/ቤቶች ነው፡፡

መቼም ዕውቀትና ሥልጣኔ የሚስፋፋው በትምህርት ቤት ውስጥ በሚሰጠው የመምህራን አስተምህሮ ነው፤ መምህራን ነቅተውና ተግተው ሲያስተምሩ፣ ትውልድም ጠንክሮ ሲማር ጥያቄ ይነሳል፤ ለጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሲባል ምርምር ውስጥ ይገባል፤

ከምርምር ውስጥ ብዙ የተሻለ ዕውቀት ስለሚገኝ የረቀቀው ጎልቶ፣ የጨለመው በርቶ እንዲታይ ይሆናል፤ አዳዲስ ሐሳቦችም እንዲፈልቁ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፤ በዚህ ሁሉ ዕውቀት ሲዳብር ሥልጣኔ ይመጣል፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን በጥንት ዘመን ከነበሩ ኃያላንና የሰለጠኑ መንግሥታት አንዷ እንደነበረች ዓለም የሚያውቀው ሐቅ ነው፤ የኢትዮጵያ መንፈሳዊና ሥጋዊ ሥልጣኔም መሠረት አድርጎ የተነሣው ሃይማኖታዊ ቅኝትን ስለሆነ መንሥኤው መንፈሳዊ ት/ቤት ነው፡፡

በቤተ መንግሥቱም ሆነ በቤተ ክህነቱ ለተከናወኑ የሥልጣኔ ሥራዎች ዋና ተዋናዮች የነበሩ ምሁራንና ጠቢባን ከመንፈሳዊ ት/ቤቶች የተገኙ ነበሩ፡፡

ሐናጺውም ሆነ ግንበኛው፣ ጸሐፊውም ሆነ አስተዳዳሪው፣ ዳኛውም ሆነ ተዋጊው፣ ቀዳሹም ሆነ አራሹ፣ ነጋሹም ሆነ አንጋሹ ከዚህ መንፈሳዊ ት/ቤት ተምሮ የወጣ ነበረ፡፡

ስለሆነም ጥንታዊቷ ኢትዮጵያን በመልካም ሁኔታ የፈጠረና ለዛሬው ትውልድ ያበረከተ ይህ መንፈሳዊ ት/ቤት ነው፡፡

2. መንፈሳዊ ት/ቤት በጥንት ዘመን

መንፈሳዊ ት/ቤት በጥንት ዘመን ከሠራቸው ዓበይት ተግባራት መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡፡

  • ከነጋሹ እስከ አራሹ ድረስ ያለውን ማኅበረ ሰብ ማስተማር
  • የሥነ ጽሑፍና የትርጉም ሥራ በስፋት መሥራት
  • የቋንቋ ሥነ ጥበብ መቀመርና ማራቀቅ
  • የሥነ ልሳን፣ የቅኔና የብሂል አነጋገርን ማዳበር
  • ድጉሰትን ቅርጻ ቅርጽን መንደፍና ሐረገ ሐረግን ማስዋብ
  • ባህርን ተሻግሮ፣ አገር ለአገር ተዘዋውሮ ያላመነውን ማሳመን ያልተጠመቀውን ማጥመቅ፣
  • ለቅዳሴ፣ ለውዳሴ የሚሆን ጣዕመ ዜማን ማቀናበርና ሐሳበ ዘመንን መተንተን
  • ኅብረተሰቡን በምግባር፣ በሃይማኖትና በተቀደሰ ባህል መቅረጽ
  • ሕዝቡ ስለሀገሩ ነጻነትና አንድነት መከበርና ስለሃይማኖቱ ህልውና መጠበቅ ጠንክሮ እንዲቆምና ሲያስፈልግም መሥዋዕትነትን እንዲከፍል ማነሣሣት በመሳሰሉት ሁሉ መ/ት/ቤቱ መተኪያ የሌለውን ታሪክ ሠርቶአል፡፡
  • በነዚህ ት/ቤቶች የተፈጠሩ መምህራንን የተመለከትን እንደሆነ የሚከተሉትን እናስተውላለን፡፡

2.1. በአክሱም ዘመነ መንግሥት የነበሩ መምህራን

በዘመነ አክሱም የነበሩ መምህራን በአብዛኛው የሠሯቸው ሥራዎች፤

  • ቅዱሳት መጻሕፍትን ከግሪክ፤ ከዕብራይስጥና ከዓረብኛ ቋንቋ ወደ ግእዝ ቋንቋ በመተርጎም ሕዝቡን ማስተማር፤
  • ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ማቀናበርና ማደራጀት /ሥርዓትና ዜማ/፤
  • ገዳማትን ማቋቋምና ሥርዓትን ማበጀት /ደብረ ዳሞ/፤
  • በሰሜን በኩል እስከ ደቡብ ዓረብና እስከ የመን እየተሻገሩ ወንጌልን በማስተማር ክርስትናን ማስፋፋትና ገዳማትን መመሥረት /ናግራንና ቅሪት/፤
  • በምዕራብ እስከስናርና መረዌ በመዝለቅ፣ በደቡብም እስከ ከፋና ዓርባ ምንጭ በመጓዝ ክርስትናን ማስፋፋት /ብር ብር ማርያም በሐጊዮርጊስ/
  • መንግሥቱ በእግዚአብሔር እንዲታመን ማሳመን /ሐውልቶች ሳንቲሞች ጦርነቶች አጼ ካሌብ/
  • የሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን ዲዛይን መንደፍና መገንባት ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን መፈልፈልና በልዩ ቅርጽ ማስዋብ /አክሱም አብርሃ ወአጽብሃ፣ ደብረ ዳሞ ቅድስት ቤተልሔም መርጡለ ማርያም/
  • የሥነ ጽሑፍና ሥነ ጥበብ ክህሎት ማሳደግ፤
  • የግእዝ ሥነ ልሳን ማዳበር፣ የጣዕመ ዜማና የቅኔ ትምህርት መድረስና ማራቀቅ /ቅዱስ ያሬድና/ ተከታዮቹ
  • ግእዝን በግእዝ በአንድምታ መተርጎም
  • የቅድስና ሕይወት መጠበቅና ማስጠበቅ በጣም ጎልተው የሚታዩባቸው ናቸው፡፡

2.2. መምህራን በዛጉዌ ዘመነ መንግሥት ከሠሯቸው ሥራዎች ጥቂቶቹ

መንፈሳዊ መብታቸው ተከብሮ እስከ ጵጵስና ድረስ መዓርገ ክህነት እንዲፈቀድላቸው መሟገታቸው /ንጉሥ ሐርቤ/፤

  • የዓባይን አቅጣጫ ለመቀየር እየዛቱ በማስፈራራት የእስክንድርያን ፓትርያርክ ከእስር ለማስፈታትና የግብፅ ክርስቲያኖችን ለመታደግ መነሣሣት /ንጉሥ ይምርሐነ ክርስቶስ/
  • አምልኮ ጣዖትን ማስወገድና ዕቁባትን መያዝ ማስቀረት /ንጉሥ ይምርሐነ ክርስቶስ/
  • በውበታቸውም ሆነ በቅርጻቸው ልዩ የሆኑ የውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሕንጻን ማነጽ /ቅዱስ ላሊበላ/
  • ክርስትናን ወደ ደቡብ ማስፋፋት ወዘተ የመሳሰሉት ጎልተው የሚታዩባቸው ናቸው፡፡

2.3. በሸዋ ዘመነ መንግሥት የመምህራን ሚና

በዚህ ዘመን በመምህራን የተሠሩ ሥራዎች

  • ሃይማኖተ አበውንና ፍትሐ ነገሥትን፣ ተአምረ ማርያምንና ሌሎች መጻሕፍትን ከዓረብኛ ወደ ግእዝ መተርጎም
  • በመሃል አገር በምሥራቅና በምዕራብ ኢትዮጵያ ገዳማት እንዲቋቋሙና ክርስትና እንዲስፋፋ ማድረግ /ዓሰቦት ደብረ ሊባኖስ የጣና ሐይቅ ገዳማት/
  • የሥነ ጽሑፍ ማለትም የድርሰት ሥራ እንዲስፋፋ ማድረግ
  • አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ አባ ኢየሱስ ሞዓ፣ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ፣ መልክዐ መልከዕ ወዘተ.../
  • የምንኩስና ሕይወት ይበልጥ እንዲጠናከር በሰሜን ኢትዮጵያ ከፍ ያለ እንቅስቃሴ ማድረግ /ደቂቀ እስጢፋኖስ/
  • ሢሦ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያን እንዲሆን ማድረግ /አቡነ ተክለሃይማኖት/
  • በመሃልና በደቡብ ኢትዮጵያ አምልኮ ጣዖት እንዲጠፉ መታገል /አቡነ ተክለሃይማኖት፣ 12 ንቡራነ እድና ሰባቱ ከዋክብት የተባሉ መነኮሳት
  • በዘመኑ ከተሠሩ ጉልህ ሥራዎች ጥቂቶች ናቸው፡፡

2.4. በጎንደር ዘመነ መንግሥት የመምህራን መሠረታዊ ተግባራት የሚከተሉት ነበሩ፡

  • የአማርኛ አንድምታ ትርጓሜ መተርጎምና ማሻሻል
  • የአቋቋም ሥነ ሥርዓት መቀመርና ማሳደግ
  • ማኅሌተ ያሬድ ይበልጥ ጥቅም ላይ ማዋል
  • የቅኔ ዜማና ቤት በልኬት መወሰን
  • ሰፊ የሆነ የሃይማኖት ተጋድሎ በማድረግ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን ሴራ ማክሸፍ /ለጨጌ በትረ ጊዮርጊስና ሌሎች ሊቃውንት/
  • ለየት ያለ የሥነ ሕንጻ ጥበብ ማስፋፋት /የፋሲል አብያተ መንግሥትና የጎንደር አድባራት/
  • የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ሥዕልና የድጉሰት ጥበብ እንዲያድግ ማድረግ
  • ጎንደርን የመንፈሳዊ ትምህርት ማዕከል ማድረግ ወዘተ የመሳሰሉት በጎንደር ዘመነ መንግሥት የመምህራን ጉልህ ሥራዎች ናቸው፤

3. ከጎንደር ዘመነ መንግሥት በኋላ እስከ አሁን ድረስ የመምህራን ተግባራት

  • ያለውን በመጠበቅ ስርጭቱን ማስፋት
  • የጵጵስና መብት ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ መታገል
  • ከኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ነጻ በመሆን በራስ መመራት የመሳሰሉት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡
  • በአጠቃላይ ከጥንት ጀምሮ ወይም ከዘመነ አክሱም ጀምሮ እስከ ጎንደር ዘመነ መንግሥት ባለው ዘመን የመመህራንነ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ዕውቀት በሽምደዳና ያለውን በመጠበቅ ብቻ ሳይወሰን ብዙ የትርጉም የፍልስፍና የማስተካከል የማሳመርና የማስዋብ ሥራ እንደሠሩ ሰናይ ከጎንደር ዘመነ መንግሥት በኋላ ግን ምንም ዓይነት የማሻሻል ሥራ ያልተሠራበት ዘመን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
  • ይህ ችግር እስካሁንም ቀጥሎ ጭራሽ ማንቀላፋት ሰፍኖአል ማለት ይቻላል፡፡

4. ለወደፊትስ ከመምህራን ምን ይጠበቃል?

  • መምህራን በሽምደዳና ባለው ላይ ብቻ በመወሰን ሳይሆን በመራቀቅ በማሻሻልና በመመራመር ያተኮረ ሥራ በመሥራት ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተማርና በመጠበቅ ላይ ያተኮረ ሥራ መሥራት ይገባቸዋል፤
  • በተለይም ያለንበት ዘመን ከትናንቱ የተለየ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፤
  • ዓለም በየጊዜው በፍጥነት እየተለወጠች ነው ይህ ሲሆን የመምህራን አማራጭ ዘመኑን በመራገምና በመቆዘም ሁሉንም ነገር በዝምታ ማለፍ ሳይሆን እሾሁን በእሾክ እንደተባለው ዓለም እሾሁን ይዛ ስትመጣ በራሷ እሾህ አጥብቆ ማጠርና አዝመራውን መጠበቅ የግድ ነው፡
  • የኛ መምህራን ዛሬ የሚታሙበት ትልቅ ጉዳይ ምንድን ነው? የሚለውን አንሥቶ ማየትም ተገቢ ነው፤ ብዙዎች ስለመምህራኖቻችን ሲናገሩ መመህራን ዝምታን የማብዛት፣ የመፋዘዝ፣ ተስፋን፤ የመቁረጥና የበታችነት ስሜት አይሎባቸዋል፤ ይህ ደግሞ ትልቅ የሞራል ውድቀት ነው፤ ፍጻሜውም አስጊ ነው እያሉ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡

ያሉን መMህራን ጥቂት ናቸው ቢባልም ያሉትስ መቼ አስተማሩ? መቼ ጻፉ? ሕዝቡንስ መቼ ጠበቁ? መቼ ተመራመሩ? የት ነው ያሉ? የሚል ጥያቄ ጎልቶ እየተነሣ ነው\ ቤተ ክርስቲያናችን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ካህናት አሏት ይባላል\ ነገር ግን መምህራኑና ካህናቱ ትውልዱን ሊያስተምሩ የሚችሉ ምሁራዊ ጽሑፎችን ጽፈው ለሕዝቡ ለንባብ ሲያቀርቡ አይታዩም፤

ታድያ የመምህራኑና የካህናቱ ዕውቀት የት ላይ ነው? እየተባለ ሐሜቱ ይነሣል፤ ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ የአንድ ዓመት ትምህርተ ሃይማኖት እንኳ በሌላቸው የሌላ እምነት ሰባክያን በየጊዜው በብዛት ሲወሰድ የኛ መምህራንና ካህናት መከላከሉ ቀርቶ ጭራሽ እስከነ አካቴው ስለችግሩ መኖር እንኳ የተገነዘቡ አይመስሉም፤

ከዘመኑ ፈሊጥና ትምህርትም በጣም የራቁ ናቸው በአጠቃላይ ውጤት አልባ ወደ መሆን እየተቃረቡ ነው የሚል ሐሳብ እየተሰነዘረ ነው፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ምንም እንኳ እንደሚባለው ባይሆንም የተነሣው አባባል ፍጹም ከእውነት የራቀ ነው ብለን ማስተባበል ግን አንችልም፤

ለምሳሌ ያህል አንድ ነገር ለመጥቀስ እንኳ ብንሞክር እውነቱን ይገልጽልናል፤ ባለፉት ዓመታት የተካሄዱ የሕዝብ ቆጠራ ውጤቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በዐሥር ዓመት ውስጥ 10 ሚሊዮን ያህል ሲቀንስ የፕሮቴስታንት ግን በ10 ሚሊዮን ጨምሮአል፤ ወይም አድጎአል፤ ይህ ለምን ሆነ? ያልን እንደሆነ የሚከተሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

ሀ/ ትምህርት ቤቶቻችንና መምህራኖቻችን በአብዛኛው በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ የተወሰኑ ሆነው ለብዙ ዓመታት ከመቆየታቸውም ሌላ በደቡብ፣ በምሥራቅ፣ በምዕራብና በመሐል ኢትዮጵያ ሕዝቡን በቋንቋው የሚያስተምሩና የሚጠብቁ መምህራንና ካህናት ከአካባቢው እንዲፈጠሩ አለማድረጋችን፤

ለ/ ይህንን ክፍተት ተጠቅመው የሌላ እምነት ተከታዮች በነዚህ አካባቢዎች በሰፊው መንቀሳቀሳቸውና ቤተ ክርስቲያናችን ሁሉን አቀፍ ሳትሆን የሰሜን ኢትዮጵያ ገዥዎች ብቻ እንደሆነች አድርገው በፖለቲካም በብሔርም በቋንቋም አመካኝተው እየተንቀሳቀሱ መስበካቸው፤

ሐ/ የመምህራኖቻችንና የካህናቶቻችን ተግባር ለአገልግሎት እንጂ ለስብከተ ወንጌል በቂ ትኩረት ያልሰጠ ሆኖ መገኘቱ፤

መ/ ከዘመኑ ትምህርት ፈሊጥና ዘዴ አለመልመድና ለአዲሱ ትውልድ ባይታወር ሆኖ መገኘት፤

ሰ/ እየመጣ ያለውን አደጋ በውል ተገንዝቦ ተገቢ የሆነ ግብረ መልስ ለመስጠት አለመዘጋጀት የመሳሰሉት ሁሉ የችግሩ ዋና መንሥኤዎች ናቸው ብለን ማየት እንችላለን ከዚህ ተነሥተን ምን እናድርግ? ወደሚለው ስንመጣ የሚከተሉትን ማየቱ ተገቢ ይሆናል፤

5. የዘመኑን ትውልድ ለመያዝ ምን እናድርግ?

  • እሾህን በእሾህ እንደሚባለው ሁሉ የዘመኑን ትውልድ በራሱ ቋንቋና በራሱ ፈሊጥ ለማቅረብና ለመያዝ የዘመኑን ትምህርት ከመንፈሳዊ ትምህርት ጋር አቀናጅቶ መማርና ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው፤
  • መምህራን መንፈሳዊ ትምህርቱን ማስተማርና ስብከተ ወንጌሉን መስበክ ቀዋሚና መደበኛ ሥራችን አድርገን መውሰድና አንዱን ካንዱ ሳናበላልጥ ሁለቱንም እኩል በእኩል በተደራጀና በተጠናከረ ስትራቴጂካዊ አካሄድ ማከናወን፤
  • የምንሰጠው ትምህርትም በመሠረተ ሐሳብና በልምምድ የታጀበ እንዲሆን ማድረግ፤
  • የስብከተ ወንጌል ሥራችን መግባባትን በሚፈጥር ዘዴ ሆኖ በተለይም ወጣቱን ትውልድ ማእከል ያደረገ ቢሆን ፤
  • የትምህርቱ ስርጭት ፍትሐዊና ሁሉን አቀፍ በማድረግ መላ ሀገሪቱን እንዲያካልል ማድረግ
  • ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠንን ግዳጅ በአዎንታ ለመፈጸም መዘጋጀት
  • የወልና የተናጠል ትምህርቶችን ለይቶ በማስቀመጥ ትምህርቱን ማስተማር
  • ዕውቀታችን በጽሑፍ ተዘጋጅቶና ወደ ሕዝብ ተሰራጭቶ በቂ ዕውቀት እንዲያስ ጨብጥ መጻሕፍትን በጥራት እያዘጋጁ ለንባብ ማብቃት
  • ካህን አጠር በሆኑ አካባቢዎች ጠንከር ያለ ሥራ ለመሥራት መንቀሳቀስ ለተከሠተው ችግር መቀረፍ የበኩላቸው አስተዋጽኦ አላቸው፤
  • ከዚህ በተረፈ እንደዛሬው የመሰለ የውይይት ስብሰባ እያዘጋጁ መነጋገሩ ጥቅሙ የላቀ ስለሆነ ልንቀጥልበት ይገባል፤

6. ማጠቃለያ

ከዚህ በላይ በአጭሩም ቢሆን ለማየት እንደሞከርነው የሃይማኖት መተንፈሻ ሳንባ መምህራን ናቸው፤ ሰው በሕይወት አለ ብለን ማረጋገጥ የምንችለው መተንፈስ ሲችል ብቻ ነው፤ ካልተነፈሰ ግን ሳንባ መተንፈሱ አቁሞአልና ሕይወት ማለፉን በዚህ እናውቃለን፡

ቤተ ክርስቲያንም በሕይወት አለች ማለት የምንችለው መምህሩ እስካስተማሩ ብቻ ነው፤ መምህራን ካላስተማሩ ሁሉም የለም፤ በጥቅም መጣላቱ ይቅርና ራሱ ጥቅሙም የለም ሃይማኖቱም የለም፤ ሁሉም ይቀራል፡፡

ከዚህ አንጻር አሁን ያለነው መምህራን በትክክል እያስተማርን ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ ቢነሣ መልሱ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፤ ነገር ግን ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራም እንደሚባለው የእስካሁኑ አብቅቶ ለወደፊቱ የተሻለና የተዋጣለት ሥራ ለመሥራት መነሣቱ የተሻለ ጥበብ ነው እንላለን፡፡

መምህራን ጥሩ የሆነ ትምህርትን አስተምረው መልካም ፍሬን ማፍራት እንዲችሉ የሚያስፈልጉአቸው ነገሮች እንዳሉ አንሥተውም፤ ሆኖም ምክንያትን እያበዙ ከማስተማር ከመገታት ይልቅ እያስተማሩ መብትን መጠየቅና የጎደለው እንዲሟላ መወትወት የተሻለ አማራጭ አድርጎ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡

መምህራን የማስተማር ግዴታቸውን በአግባቡ ለመወጣትና መብታቸውን ለማስከበር መሰባሰብ፣ መጠያየቅና መደራጀት ያስፈልጋቸዋል፤

ይህም በዘፈቀደ ሳይሆን በተፈቀደው መዋቅር ማለትም በቃለ ዓዋዲው ደምብ መሠረት በአጥቢያ ደረጃ በትምህርት ክፍሉ አማካይነት፣ በወረዳ፣ በሀገረ ስብከትና በጠ/ቤ/ክህነትም በተመሳሳይ ከዚያም ዓመታዊ ጉባኤ በማካሄድና ሥራቸውን በአጠቃላይ በመገምገም የተሻለ የሥራ ለውጥ ማምጣት ይገባቸዋል፡፡

ይህንንም የትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያና የካህናት አስተዳደር መምሪያ የጋራ መርሐ ግብር በማውጣት ሊመሩትና ሊያጠናክሩት ይገባል፤ ይህ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚታይ ጉልህ የሥራ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡

"ንባርኮ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ"
አሜን
ሰኔ 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ
የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ

Read more http://eotcssd.org/ethiopian-orthodox-tewahedo-church-monasteries/55-2011-03-31-12-45-49/385-2014-07-04-05-56-58.html