ለልብ ሕመም አስጊ የሆኑ ዐበይት መነሻዎች ምንድን ናቸው?

ለልብ ሕመም አስጊ የሆኑ ዐበይት ጉዳዮች በሦስት ይመደባሉ፦

- ቀደም ብለው ያሉ በሽታዎች (የታማሚው ሰው ጤንነት)

- ፀባይ (የታማሚው ሰው የአመጋገብ ሁኔታ እና አኗኗሩ)

- ቤተሰብ ሊመጣ የሚችል በሽታ (የቅርብ ቤተሰብጤንነት)

 

፩ኛ- ቀደም ብለው ያሉ በሽታዎች (የታማሚው ሰው ጤንነት) 

በደም ውስጥ ያለው የኮሌስተሮል መጠን

ኮለስትሮል በጉበት ውስጥ ወይም በተወሰኑ የምግብ ዓይነቶች አማካኝነት የሚዘጋጅ ቅባትነት ያለው ንጥረ ነገር ነው። ይኽ ቅባትነት ያለው ንጥረ ነገር ለሰውነታችን አስፈላጊ ነው። ጉበታችንም ለሰውነታችን የሚያስፈልገውን መጠን ያህል ያዘጋጃል። የኮሌስተሮል መጠን አመጋገብና ኮሎስትሮል ከአስፈላጊነቱ በላይ ለሰውነታችን ጥቅም አለመመጣጠን የተነሳ የኮሌስተሮል ክምችት ይፈጠራል - ይኽም ትርፍ ኮሌስተሮል ወደ ልባችን ደም በሚያመላልሰው ቱቦ ውስጥ ይከማቻል ወይም ይለጠፋል። ይኽ ሁኔታም የደም ማመላለሻ ቧንቧዎች ያጠባል፤ ለልብ ሕመምና ለተለያዩ ውስብስብ የጤና ቀውስ ያጋልጣል።

አንዳንድ ኮሌስተሮል"ጥሩ" እና "መጥፎ" በመባል ይታወቃል። ከፍተኛ ክብደት ያለው high–density lipoprotein cholesterol, or HDL, "ጥሩ" ተብሎ ይመደባል። ይኽም የልብ ሕመምን ለመከላከል ያስችላል። በአንፃሩም ዝቅተኛ ክብደት ያለው low–density lipoprotein, or LDL, "መጥፎ" በመባል ይታወቃል። ይኽኛው ደግሞ ለልብ ሕመም ያጋልጣል። እነኝህን ለማወቅ የተለያዩ ኮሌስተሮል ዓይነቶችን ለመለካት ይቻላል።

· ከፍተኛ የደም ግፊት

ለልብ ሕመም ሌላው ዐቢይ መነሻ የሚሆነው ከፍተኛ የደም ግፊት ነው። ይኽም ሁኔታ የሚከሰተው በደም ማመላለሻ ቱቦ ውስጥ የደም ግፊት ከፍተኛ ሆኖ ሲገኝ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ለከፍተኛ የደም ግፊት ምንም ዓይነት የሚታወቅ ምልክት አይኖረውም። የአኗኗር ሁኔታን በመለወጥ እና ሕክምና በመከታተል የደም ግፊትን መቀነስ የልብ ሕመምን እና ድንገተኛ የልብ ሕመምን (Heart Attack) እድል ዝቅ ማድረግ ይቻላል።

· የስኳር በሽታ

የስኳር በሽታ ልብ ሕመም የመጠቃታችንን ሁኔታ/እድል ከፍ ያደርገዋል። የስኳር በሽታ ካለ ሰውነታችን በውስጣችን ያለውን የስኳር መጠን ወደ ህዋሶቻችን እንዲገባ የሚያደርገውን ቁልፍ ወይም ኢንሱሊን (insulin) ማዘጋጀት አይችልም ወይም ስኳርን ለህዋሶቻችን እንድንጠቀምበት የሚረዳንን ንጥረ ነገ ማለትም ኢንሱሊንን መጠቀም አይችልም ማለት ነው። ይኽ ሁኔታ ደግሞ በደማችን ውስጥ የስኳር መጠን እንዲጠራቀም/ ከፍ እንዲል ምክንያት ይሆናል። ሦስት አራተኛ (3/4)የሚሆኑ የስኳር በሽታ ታማሚዎች በተለያየ ዓይነት የልብ እና የደም ስሮች (blood vessel)  ሕመም ምክንያት ይሞታሉ። ለስኳር በሽታ ታማሚዎች ከጤና ባለሙያ ጋር መነጋገር በሽታውን ለመቋቋምና ከሌሎች አስጊ ሁኔታዎች ለመዳን ያስችላቸዋል።  

- ፀባይ፦

· ትምባሆ (ሲጋራ) ማጨስ

ትምባሆ መጠቀም የልብ ሕመምን እና ድንገተኛ የልብ ህመም ሁኔታ እንዲጨምር ያደርጋል። ሲጋራ ማጨስ በደም ቱቦ ውስጥ የሚገኙትን ደማችን እንዳይፈስ/ እንዲረጋ የሚያደርገውን ንጥረ ነረር (fibrinogen) ከአስፈላጊው በላይ ከፍ እንዲሉና የደም መርጋትንም ሁኔታ እንዲባባስ ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪም በሲጋራ ውስጥ የሚገኘው ኒኮቲን (nicotine) የደም ግፊትን ያስነሳል፤ ካርበን ሞኖክሳይድም/ መርዛማ አየር (carbon monoxide) ደማችን ሊሸከም የሚገባውን ኦክስጅን/ጥሩ አየር እንዲቀንስ ያደርገዋል።  የሲጋራ ጭስን ወደማያጨሱ ሰዎች ማስተላለፍ/መበከል የማያጨሱትን ሰዎች እንኳ ለከፍተኛ ልብ ሕመም እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል።

· አመጋገብ

የተለያየ ዓይነት የአመጋገብ ሁኔታ ከልብና ከልብ ጋር ተመሳሳይነት ካላቸው በሽታዎች ጋር ይገናኛል። ከእነዚህ የምግብ ዓይነቶች መካከል ከፍተኛ የቅባት ጥርቅም ያላቸው ምግብ ሲሆኑ እነዚህም ምግቦች በደም ውስጥ የኮሌስተሮል መጠንን የሚጨምሩና የደም ማመላለሻዎች መጠጠርና መጥበብ  (atherosclerosis ) የሚያመጡ ናቸው። በምግብ ውስጥ ከፍተኛ ጨው ወይም ሶድየም (sodium) መኖሩ የደም ግፊት መጠንን ከፍ እንዲል ያደርጋል።

· የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ለልብ በሽታ ማደግ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የአካል እንቅስቃሴ መቀነስ ሌሎች አስጊ ሁኔታዎች እንደ ሰውነት ክብደት መጨመር፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ከፍተኛ የደም ቅባት ዓይነት (triglycerides) የጥሩው ኮሌስተሮል መጠናችን መቀነስ HDL (good) cholesterol እና ስኳር በሽታ ጋር ይያያዛል። በአንጻሩ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለበሽታው አስጊ ከሆኑት ነገሮች መከላከል ያስችላል። መጠን አልባ የሆነ የሰውነት ክብደት መጨመር፦ እንዲህ ያለው ክብደት የተትረፈረፈ የስብ ጥርቅም በሰውነት ላይ ሲታይ እና ሲገኝ ነው። ይኽውም ያለ ቅጥ ክብደት መጨመር ከመጥፎ ከሚባለው ኮሌስተሮል መጨመር (LDL) እና ሌሎች ከመጠን በላይ የሆኑ የደም ውስጥ የቅባት መጠን (triglycerides) መጨመር አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከከፍተኛ የደም ግፊት እና የስኳር በሽታ ጋር የተያያዘ ነው።

· አልኮል

ብዙ አልኮል መጠጣት የደም ግፊትን ይጨምራል፤ ለልብ ሕመምም አስጊ ሁኔታን ይፈጥራል። ከዚህ በተጨማሪም triglycerides የደም ውስጥ ያለ የቅባት መጠንን ይጨምራል። ይኽም ለደም መመላለሻዎች መጠጠርና መጥበብ  (atherosclerosis) አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ተከታዩ ክፍል በሚቀጥለው ዕትማችን ላይ ይወጣል።

ይስሐቅ ቱራ (RN)