ከሕፃናት እና  ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ (መዝ.  ፰፡፪ )

ቅዱስ! ቅዱስ! ቅዱስ! እግዚአብሔር እያሉ የሚያመሰግኑ የሰማይ መላእክት በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት የመቆምን ዕድል አግኝተው ምስጋና ገንዘባቸው ሆኖ ሲያመስግኑ ይኖራሉ። ሕፃናትም ለአምላካቸው ሚያቀርቡትን ድንቅ ምስጋና አስመልክቶ ኢየሱስ ክርስቶስ ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ" የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን?  እንዳላቸው ተጽፎ እናነባለን። ቤተ ክርስቲያን ለሕፃናት ተገቢውን ሥፍራ ሰጥታ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አምላካቸውን ቀርበው እንዲያመሰግኑ በተለየ እንክብካቤ የምትመለከታቸው አስቀድሞ የወደዳቸውና የምስጋና አንደበትን የሰጣቸው እርሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ ነው።

ሕፃናት በልዑል እግዚአብሔር ፊት የሚወደዱና እግዚአብሔር ለሕዝቡ  የሚፈልገው ዓይነት ልበ ንጹሕ ሆነው በመገኘታቸው ፈሪሳውያን ጌታችንን ሊፈትኑት ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት በሰጣቸው ምላሽ ላይ ሕፃናትን ተዉአቸው፥ ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉ ናትና  (ማቴ. ፲፱፡፲፫-፲፭) በማለት ሲናገር እንሰማዋለን። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጌታችንን አስተምህሮ በመከተል ሕፃናትን እያስተማረችና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገቢውን እንክብካቤ እያደረገች ዛሬ በደረስንበት ደረጃ ላይ እንድንታይ አስችላናለች።

ዛሬም የታላቁ ደብር የርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመቼውም በበለጠና በተሻለ እንቅስቃሴ ሕፃናቶችንና አዳጊ ወጣቶችን በሳምንት ሁለት ጊዜ ቅዳሜና እሑድ የወንጌል እና የአብነት ትምህርት በማስተማር ሕፃናት ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲወዱና ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲያውቁ ታላቅ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች። በዐውደ ምሕረት ላይ በተለያዩ ዕድሜ ላይ ያሉ ሕፃናት እና ወጣት ልጆቻችን ዝማሬ ለማቅረብ በእግዚአብሔር ፊት በየሳምንቱ ይቆማሉ። የነገዪቱ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢዎች የዛሬዋ ሕፃናት ሊሆኑ የሚችሉት ገና ከአሁኑ በዚህ ዕድሜያቸው በፈሪሐ እግዚአብሔር ታንጸው ቤተ ክርስቲያንን ማወቅ ሲችሉ ብቻ ነው። የተጀመረው ትምህርት ሳይቋረጥና እየታየ

ያለው እንቅስቃሴ ሳይዳከም መራመድ ከቻልን እግዚአብሔር የወደዳቸውንና መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ምሳሌ ያደረጋቸውን ሕፃናት ከአሁኑ በበለጠ በመንከባከብ ማንነታቸውን ልናሳውቃቸው እንችላለን። ሕፃናት የነገሯቸውን አይረሱምና ቶሎ ለመማርም አእምሯቸው ፈጣን ነውና ጊዜ በማጥፋት መልካሙን ሁሉ ልናስተምራቸው የሚገባን በአሁኑ ሰዓት ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን ለሕፃናት ትምህርት የሚያስፈልገው በጊዜ መሆኑን ሲያስረዳ ፦ ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፥ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም። (ምሳሌ ፳፪፡፮) ይለናል።

 

በወ/ ሰብለወንጌል ደምሴ