በአብ ስም አምኜ አብን ወላዲና አሥራጺ ብዬ፤ በወልድ ስም አምኜ ወልድን ተወላዲ ብዬ፤ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኜ መንፈስ ቅዱስን ሠራጺ ብዬ ምንም ለአጠይቆ አካላት ሦስት ብል በመለኮት በሥልጣን በአምላክነት አንድ አምላክ ብዬ አምኜ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ስለ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያገኘሁትን መጻፍ እጀምራለሁ። አምላካችን እግዚአብሔር ለአባቶቻችን ምሥጢሩን እንደገለጸ ለእኛም ይግለጽልን አሜን።

"በዓመት በዓመት በየወራቱ ይኽቺን ሥርዓት ጠብቃት"(ዘጸ. ፲፫፡፲)። ይኽንን ቃል የምናገኘው እስራኤል ከግብፅ የመውጣታቸው ዜና በተጻፈበት መጽሐፍ ነው። ሥርዓትንም ሠርቶ የሰጣቸው በባርነት ሳሉ ሳይሆን ወደ ነፃነት ምድር በመሄድ ላይ ሳሉ ነው። አምላካችን እግዚአብሔር ያዘጋጀልንን መንግሥቱን ያወርሰን ዘንድ ሲወድ የምንመራበትን መመሪያ የምንሠራውንም ሥራ መቼ እና እንዴት ማከናወን እንደሚገባን ሊያሳውቀን ሥርዓትን ሠራልን። የሠራልንን ሥርዓት ደግሞ ዘወትር ልንፈጽመው እንጂ ጊዜና ሁኔታ እየጠበቅን ሥርዓቱን እንዳንተውና እንዳናቃልል በየወራቱና በየዓመታቱ መጠበቅ እንደሚገባን በአጽንዖት ተናገረ። ሥርዓትን ለመጠበቅ ግን መጀመርያ "ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን" ምን እንደሆነ ማን እንደሠራውና ጥቅሙን ማወቅና መረዳት ይበጃል። ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ከማየታችን በፊት ግን ለሁላችንም ግልጽ ሊሆንልን የሚገባው ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ቃል ትርጉምና ምንነት ነው። ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል ሦስት ትርጉም እንዳለው የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይገልጹታል፦

፩) የክርስቲያኖች አንድነት ወይም ስብስብ (ዕብ. ፲፪፡፩)

፪) የክርስቲያን ሰውነት (፪ ቆሮ. ፮፡፲፮፤ ሐዋ. ፲፩፡፳፮)

፫) ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን (ሉቃ. ፩፡፳፩፤ኢሳ.፵፬፡፳፰)

ከእነዚህ ከሦስቱ የመጀመርያውን ወስደን ምን ማለት እንደሆነ እንመለከታለን። በክርስቶስ ኢየሱስ ጌትነት ፍጹም የባሕርይ አምላክነትና ፍጹም ሰውነት የሚያምኑና የሚታመኑ ሁሉ ክርስቲያን ወይም ክርስቶሳውያን ይባላሉ። ስለዚህም መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበረ።

(ማቴ. ፬፡፲፩) ስለዚህ መላእክት ከክርስቲያን ማኅበር ናቸው ማለት ነው። ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። (ኢሣ. ፱፡፮) ነቢያትም ከዚሁ ሕብረት ናቸው። ...ቅዱስ መጽሐፋችንም “ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ።” (ሐዋ. ፲፩፡፳፮) ይለናል። ስለዚህ በሥጋም በነፍስም በመንፈስም ያሉ የክርስቶስ አማኞችና አገልጋዮች ሕብረት አንድነት ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ይጠራል።

የቤተ ክርስቲያን ትርጉም እንዲህ ከሆነ ሥርዓት ምንድር ነው? ሥርዓት ማለት ሠርዓ ሠራ ካለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ሥርዓት አሠራር አፈጻጸም መመሪያ ማለት ነው። በመሆኑም ሥርዓት የቤተ ክርስቲያንን ሕግጋት የምንፈጽምበት (የምንሠራበት) መመሪያ ማለት ነው።  አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ሥርዓትና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ዛሬ አዝዞሃል፤ አንተም በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ጠብቀው፥ አድርገውም። (ዘዳ. ፳፮፡፲፮) ስለዚህ ሥርዓት ማለት ልንጠብቀውና ልንፈጽመው የሚገባና በሆነውም ባልሆነውም የሚቀየርና ሲመች የሚፈጽሙት ሳይመች የማይፈጽሙት አይደለም። ሥርዓት ማለት በመላእክት ተራዳኢነት በቅዱሳን ጸሎት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በቅዱሳን አባቶች (በቅዱስ ሲኖዶስ) የሚሠራ እንጂ እንደ ዓለማውያን መመሪያ በዚህ ይስተካከል ይኼ ይቀነስ ወይም ይጨመር የማይባል ነው። (፪ ጴጥ. ፩-፳) ስለዚህ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን አባቶች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የሚሠሩትና ዘመናትን ተመልክተው የሚጨመረውን እየጨመሩ የሚሻሻለውን እያሻሻሉ የሚቀጥል እንጂ የሚቀነስ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የለም። ማንም የራበው ቢኖር ለፍርድ እንዳትሰበሰቡ በቤቱ ይብላ። የቀረውንም ነገር በመጣሁ ጊዜ እደነግጋለሁ። (፩ ቆሮ. ፲፩፡፴፬) ይኽንን ያህል ስለ ሥርዓት ካልን በቤተ ክርስቲያን ስለሚፈጸሙ ሥርዓቶች ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሚቀጥለው ጽሑፍ እንገናኛለን። አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን በአንድነት በሦስትነት ለሚመሰገን ለሥላሴ ክብር ምስጋና ይሁን አሜን።

መጋቤ ኅሩያን ቀሲስ መጽናኛዬ ኃይሌ