በአምላካችን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም በተመሠረተችው እና ሐዋርያት ባጸንዋት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለያዩ ጊዜ የተነሡትና በተለያዩ ጊዜያት ጉባኤ ዘርግተው ሃይማኖታዊ ውሳኔ የደነገጉት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በጸሎተ ሃይማኖት ላይ "ከዚህ በኋላ በሥጋ ታመመ፣ ሞተ፣ ተቀበረ..." በማለት ሕማሙንና ሞቶ መቀበሩን ከጻፉልንና ካስተማሩን በመነሣት አባቶቻችን ከሆሣዕና ማግስት ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ዋዜማ ያሉትን ቀናት"ሰሙነ ሕማማት" ብለው ሰይመውታል። በመሆኑም እኛም አባቶቻችን በእነዚህ ስድስት ቀናት የጌታችንን ሕማሙን በማሰብ በታላቅ ጸሎት፣ ስግደትና ጾም እንድናሳልፍ መጽሐፍ ጽፈው፣ ጸሎት አዘጋጅተውና ሥርዓት ሠርተው ሰጥተውናል። እያንዳንዱ የዓቢይ ጾም ሳምንት የእራሱ መጠሪያ እንዳለው እነዚህም ስድስት ቀናት የየእራሳቸው የሕማሙና የሞቱ መታሰቢያ ስላላቸው እንደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ክንዋኔአቸውን በአጭሩ እናቀርባለን፦

 

 ሰኞ፦ በዚህ የመጀመርያው ዕለት

+ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቢታንያ ወደ ቤተ መቅደስ ማምራቱ፤

+ ፍሬ አልባ የሆነችውን በለስ መርገሙ (ማቴ. ፳፩ ማር ፲፩)፤

+ ቤተ መቅደሱን ከገንዘብ ለዋጮች ማንጻቱ፤

+ በቤተ መቅደስ ማስተማሩና ተአምራት ማድረጉ እንዲሁም በቢታንያ ማደሩ ይነገራል።

 

ማክሰኞ፦ በዚህ በሁለተኛው ዕለት

+ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱና የረገማት ቅጠል ከነሥሯ ደርቃ እንዳያት፤

+ ለሕግ ጠባቂዎችና መምህራን ፈሪሳውያንና የአይሁድን ትምህርት ለተማሩ የጥቂት ሰዱቃውያንን ጥያቄ መመለሱ፤

+  ስለ ዳግም ምጽአቱና ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ ማስተማሩ፤

+ ስለ ወይኑ ቦታና ስለ ሠራተኞቹ፣ (ማቴ. ፳፩) ስለ ንጉሡ ልጅ ሠርግ(ማቴ. ፳፪) ስለ ልባሞቹና ስለ ሰነፎቹ ደናግል በምሳሌ ማስተማሩ፤

+ በድጋሚ ወደ ቢታንያ ስለ መመለሱ ይነገራል። (ማቴ. ፳፮)

 

ረቡዕ፦ በዚህ በሦስተኛው ዕለት

+ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሙሉ ቀን በቢታንያ ስለማሳለፉ፤

+ ኃጢአተኛዋ ሴት መዓዛው የጣፈጠ ሽቱ በጌታችን ላይ ስለማፍሰስዋ

     (ማቴ. ፳፮) (ይኽቺም ሴት በጌታችን እግር ላይ ዘይት እያፈሰሰች በፀጉሯ ያበሰችው የአልዐዛር እኅት ማርያም አይደለችም) እና

+ የአስቆሮቱ ይሁዳ በሠላሣ ዲናር ጌታን አሳልፎ ለመስጠት ከአይሁድ ጋር መስማማቱ፤

+ ካህናተ አይሁድ ሊይዙት መምከራቸው ይነገራል።

 

ሐሙስ፦ በዚህ በአራተኛው ዕለት

+ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ለፋሲካ የሚሆነውን እራት እንዲያዘጋጁ ነግሯቸው ስለማዘጋጀታቸውና የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ የምሥጢረ ቁርባንን ሥርዓት መሥራቱ፦ እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ ቆርሶም ሰጣቸውና። ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ። ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።(ሉቃ. ፳፪፡፲፱-፳)

+ የኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ጸሎት ማድረግ፦ አባት ሆይ፥ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። (ሉቃ. ፳፪፡፵፪) መባሉ ይነገራል።

 

አርብ፦  በዚህ በአምስተኛው ዕለት

+ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳም በበደለ ጊዜ ከሳሽ ዲያብሎስን በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ። (ዘፍ. ፫፡፲፭) በማለት የገባለት ቃል መፈጸሙ፤

+ ስለ ጌታ መያዝ፣ መገረፍ፣ መሰቃየትና መሰቀል ይነገራል። በቤተ ክርስቲያንም ከሰኞ እስከ ሐሙስ ከሚደረገው ስግደት በበለጠ ነገረ መስቀሉን በማሰብ በጸሎትና በስግደት ዕለቱ ይከበራል።

 

ቅዳሜ፦ በዚህ በስድስተኛው ዕለት

+ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሙታን እንደሰበከላቸው በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ (፩ጴጥ. ፫፡፲፰) እንዲል።

ከዚህ በተጨማሪም በኖኅ ዘመን ስለ ውኃው መጉደል ርግብ የለመለመ ቅጠል ይዛ እንደመጣች የቅዳሜ ስዑር ዕለትም ካህናት "ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላምን አደረገ።" በማለት ለሕዝቡ የለመለመ ቄጠማ ያድላሉ። ምክንያቱም በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትም የኃጢአት ባሕር እንዲሁ ተወግዷልና። ይኽ ዕለት ቅዳም ስዑር ይባላል። ትርጓሜውም "የተሻረ" ማለት ነው። ይኸውም ቅዳሜና እሑድ ጾም የማይገባ ሆኖ ሳለ ጌታ በከርሠ መቃብር ስላደረ በአክፍሎት ስለሚጾም ቅዳም ስዑር ይባላል።  

 

እንበለ ደዌ ወሕማም፤ እንበለ ፃማ ወድካም፤ ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በፍሥሐ ወበሰላም።

 

 ሊቀ ብርሃናት ቀሲስ ሄኖክ ያሬድ