ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ቅድስት ቤተ ክርስትያን ከምትጠቀምባቸው ለበሽተኞች የፈውስ መንገዶች ጸበል ዋነኛው ነው። ጸበል የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት በመሆኑ ብዙዎች ሰዎች ከአጋንንት እሥራት፣ ከጭንቀት፣ ልጅ አልባ ከመሆን፣ ከሱሰኝነት፣ ከመንፈሳዊ ዝለት ነጻ የሚወጡበት ፍቱን የእግዚአብሔር በረከት ነው። ጸበል የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት ቤታችን ከምንጠቀምበት የተለየ ውኃ ነው። "የእግዚአብሔር መንፈስ በውኃው ላይ ሰፍፎ ነበር።" እንዳለ ዘፍ ፭ ፤ ፫

አምላካችን እግዚአብሔር በነብያቱ  አድሮ ሕዝቡን ሲያጽናና ፣ ሲመክር፣ ሲገስጽ፣ ሲያበረታ የነበረ መሆኑ እሙን ነው። እንዲህም ብሎ ደግሞ መንፈሳዊ በረከትን የሚያገኙበትን መንገድ ያሳያቸው ነበር። ጥሩ ውኃም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላች ከርኩሰታችሁም ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ" ሕዝ ፴፮ ፤ ፳፭

እንግዲህ ይህ ልዩ የሆነ ከተለያዩ ውጣ ውረዶች ነፃ የሚያወጣው ጸበል ለብዙ ሰዎች እረፍት፣ መረጋጋት፣ መጽናናት፣ ከአጋንንት ወጥመድ ነፃ መውጣት፣ ከተነከሩበት ባዕድ አምልኮት መላቀቅ መንፈሳዊ ኃይል ሆኖ እናገኘዋለን፤ ይኸውም  በመጠመቅና በመጠጣት ነው። የውስጥ ደዌ ያለበት ደግሞ በመጠመቅ ይድናል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን በልዩ ልዩ ሁኔታ ሰዎች የሚያገኙትን እንዳያገኙ፤ ልጅ እንዳይወልዱ ማድረግ፣ እንዲጨነቁ  እንዲጠበቡ ማድረግ  ዋነኛው እንደሆነ ያስረዳናል። በኢያሪኮ ከተማ ነብዩ ኤልሳዕ በገባ ግዜ የሰማው ዜና ውኃው ሴቶችን መውለድ እንዳይችሉ ያደርጋል የሚል ጩኸት ነው።

ነብዩ ኤልሳዕ "አዲስ ማሰሮ አምጡልኝ፤ ጨውም ጨምሩበት" አለ ያንንም አመጡለት። እርሱም ውሃው ወዳለበትም ምንጭ ወጥቶ ጨው ጣለበትና እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ይህን ውኃ ፈውሼዋለሁ ከዚህም በኋላ ሞትና ጭንጋፍ አይኾንበትም አለ። ኤልሳዕም እንደተናገረው ነገር ውኃው እስከ ዛሬ ድረስ ተፈውሷል። ፪ነገ  ፪ ፤፲፱-፳፪ ለዚህም ነው ከላይ እንደገለፅነው የጸበሉ ባለቤት እግዚአብሔር ሲሆን መታሰቢያነቱ ግን በቅዱሱ ፣ በሰማዕቱ፣ በነብዩ፣ በሐዋርያው፣ በመላዕክቱ፣ ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ በሆነችው በእመቤታችነ ነው። ነብዩ ኤልሳዕም የተናገረው ይህን ውኃ እግዚአብሔር ፈውሼዋለሁ ብሏል ነው። ዛሬም ቅዱስ ጸበል ያልወለዱትን እንዲወልዱ፣ የታመሙት እንዲድኑ ያደርጋል። የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ የነበረው ንዕማን ከለምጽ ነፃ የሆነው ከዮርዳኖስ ወንዝ ሰባት ግዜ ብቅ ጥልቅ እያለ በመጠመቁ እንደሆነ መፅሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። "ንዕማንም ከንጉሡ ደብዳቤ አጽፎ ወደ ነብዩ ኤልሳዕ በፈረስና በሰረገላ ሆኖ መጣ። በኤልሳዕም ቤት ደጃፍ ውጭ ቆሞ ኤልሳዕም ሂድ በዮርዳኖስ ሰባት ግዜ ታጠብ፤ ሥጋህም ይፈወሳል ፤ አንተም ንፁህ ትሆናለህ ብሎ ወደርሱ መልዕክቶች ላከ።

ንዕማን ግን ተቆጥቶ ሄደ። እንዲህም አለ፤ እነሆ ወደ እኔ የሚመጣ፣ ቆሞም የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ፣ የለምፁንም ሥፍራ በእጁ ዳሶ የሚፈውስ መስሎኝ ነበር። የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋ በእነርሱ መታጠብና መንፃት አይቻለኝም ኖሯልን? ብሎ ተቆጥቶ ነበረ። ... የእግዚአብሔርም ሰው እንደተናገረው በዮርዳኖስም ሰባት ግዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ኾኖ ተመለሰ፤ ንጹሕም ሆነ።" ፪ነገ ፭ ፤ ፩-፲፮ 

በሐዲስ ኪዳንም ከመወለዱ ጊዜ አንስቶ ዓይነ ሰውር ብቻ ሳይሆን የዓይን ሥፍራ እንኳን ቦታ ያልነበረው የአይሁድ ማኅበረ ሰብን ብቻ ሳይሆን ሐዋርያትን ሳይቀር እንደዚህ ሆኖ መወለዱ በማን ኃጥያት እንደሆነ እንዲጠይቁ ያደረጋቸው የአለማየቱን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የዓይን ስፍራ ያለመኖሩ ነበረ። ጌታችን ግን ያለው የእግዚአብሔር ሥራ ይገለጥ ዘንድ አለና ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው፤ እያየም መጣ ። ዮሐ ፱ ፤፮ ጸበል የእግዚአብሔር ሥራ መገለጫ መንገድ እንደሆነ ያስገነዝበናል።

በሌላ መልኩ በዮሐንስ ወንጌል እንደምናገኘው በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች። አምስት መመላለሻ ነበረባት፤ በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች ፣ አንካሶችም ሰውነታቸው የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበረ። አንዳንድ ግዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበር። እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ መጀመሪያ የገባ ከማንኛውም ደዌ ተላቆ ጤነኛ ይሆን ነበር። የሐዋ ፭፤፪-፬

ከዚህም ላይ የምንመለከተው ወደ መጠመቂያይቱ መጀመሪያ የገባ ከማናቸውም ካለበት ደዌ መዳን ይችል እንደነበረ  ይነግረናል ። ብዙዎች የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ በጸበል ይመለከቱ ይድኑም ፤ ይፈወሱም ነበርና። 

ዛሬም ብዙዎች ጸበል እየዳኑ ፣ እየተፈወሱ ፣ ከልባቸው ጭንቀት ነፃ እየወጡ፣ የታመሙ እየዳኑ ፣ ዕውሮች እያዩ ፣ጎባጦች እየቀኑ ፣ ልዩ ልዩ ደዌ ያለባቸው ፍጹም ፈውስ እያገኙበት ይኖራሉ ፤ ወደፊትም እንዲሁ በጸበል ለመዳን አምኖ መገኘት አስፈላጊ ነው። ለመጠመቅ ደግሞ አመቺ ጊዜን ወስኖ በጸሎት እና ልመና ንስሐ በመግባት ፈጣሪን እየተማጻኑ መጠመቅ  ተገቢ እንደሆነ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ታስተምራለች።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር

መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ስንታየሁ ደምስ