ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ንኡሳን በዓላት መካከል እነዚህ ሦስቱ በዓላት በዘመነ ስብከት ከታኅሳስ ፯ እስከ ታኅሣስ ፳፯ ድረስ ባሉት ሦስት እሑዶች ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ ተብለው  ተሰይመው በቤተ ክርስቲያናችን የመዝሙርና የጸሎት ሥርዓት ይከበራሉ። የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ነቢያት አምልተውና አስፍተው በትንቢት ያስተማሩበት፣ የሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበት፣ የምሥራቹ የተነገረበት ወቅት በመሆኑም በኢ//// ሊቃውንት አስተምህሮ ዘመነ ስብከት ይባላል።

በእነዚህ ሳምንታት ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው በትንቢት ይጠባበቁት የነበረው መሲህ የዓለም ብርሃን፣ የነፍሳት ጠባቂ ነው በማለት ነቢያት ያስተማሩትንና የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ለሦስቱ እሑዶች የሰጡትን ስያሜ እንመለከታለን፤

ስብከት

ስብከት ማለት ማስተማር /ትምህርት/ ማለት ነው፤ በዚህ ሳምንት ከልደተ አብርሃም እስከ ልደተ ዳዊት ያለው ትውልድ የሚታሰብበት፤ ሙሴ በኦሪት፣ ነቢያት በትንቢት፣ ዳዊት በመዝሙሩ በብዙ ምሳሌ ይወርዳል ይወለዳል ሲሉ ስለ ክርስቶስ ሥጋዌ /ሰው መሆን፣ ሥጋ መልበስ/ ትንቢት ተናግረው፣ ምሳሌ መስለው፣ ሱባዔ ቆጥረው የክርስቶስን መምጣት አስቀድመው በማስተማር ሰብከውት ነበር ለማለት ቀኑ /ሳምንቱ/ ስብከት ተባለ።

¨ እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም ከብዙ ውኆች፥ አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር፥ ቀኛቸው የሐሰት ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ። (መዝ ፻፵፫ ፯)

¨ ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። (ኢሳ፣ 714)

¨ ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ! (ኢሳ ፷፬፥፩)

¨ አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል። (ሚክ ፭፥፪)

 

ከዚህ በላይ ባሉት ጥቅሶች እንደምንረዳው ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው በሰፊው አስተምረዋል፤ ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ "ንህነሰ ንሰብክ ክርስቶስሃ ዘተሰቅለ" ትርጉም፦"እኛስ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን" (፪ቆሮ ፬፥፭)

ቅዱስ ያሬድም በመዝሙሩ "ወልዶ መድኅነ ንሰብክ ዘእምቅድመ አለም ሀሎ" ትርጉም፦"ከዓለም በፊት የነበረውንና መድኃኒት የሆነውን ወልድን እንሰብካለን" እንዳለ መቼም ቢሆን መች፣ በጊዜውም አለጊዜውም፣ ሲሞላም ሲያጎድልም ስለ ኃጢአታችን የሞተውንና መድኃኒት የሆነውን ክርስቶስን ልንሰብክ ይገባል።

ብርሃን

ነቢያት የአምላክን ማዳን ከጠበቁባቸውና፣ ከገለጡባቸው መንገዶች አንዱ ብርሃን ነው፤ በዚህ ሳምንት ከልደተ ዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን ያለው 14 ትውልድ ይታሰቡበታል፤ ከዚሁ ጋር ዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ፣ መከራ ነፍስ የፀናበት የሰው ልጅ ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት ስለነበር ነቢያት ያሉበትን ያን ዘመን ጨለማ ብለው በመግለጥ የነፍሳችን ብርሃን ይወለዳል፣ እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ስለመስበካቸው የሚታሰብበት ቀን/ሳምንት/ ነው። ለምሳሌ፦ መዝሙረኛው ዳዊት ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራ ብርሃን ወደ ዓለም እንዲመጣ እንዲህ ብሎ ይጸልይ ነበረ "ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ" ትርጉም፦"ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ" (መዝ ፵፪፥፫) የዚህ ቃል የምሥጢር ትርጉሙ ብርሃን፣ ጽድቅ፣ እውነት ልጅህን (ወልድን) ላክልን እርሱ መርቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት ያስገባን ዘንድ ማለትነው። (ኢሳ ፵፱፥፮) (ዮሐ ፩፥፩-፲፱) (ዮሐ ፰፥፲፪) በዚህ ዕለት "ብርሃን ዘኢይትነገር" የማይነገር ብርሃን የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ብርሃን መሆኑ ይሰበካል፤ "ብርሃን ዘመጽአ ውስተ አለም"ብርሃን ወደ አለም መጣ እየተባለ በቅዱስ ያሬድ መዝሙር ይመሰገናል።

ኖላዊ

ኖላዊ ማለት እረኛ ማለት ነው። ነቢያት ራሳቸውንና ሕዝበ እስራኤልን ብሎም ዓለምን እረኛቸው እንደተዋቸው በጎች በመቁጠር እውነተኛ እረኛ ሆኖ የእግዚአብሔር ልጅ ይገለጣል ብለው መተንበያቸውንና ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ እረኛ መሆኑን እያሰበች ቤተ ክርስቲያን የምትዘምርበት፣ የምትቀድስበትና፣ የምታመሰግንበት ወቅት ነው። በዚህ ጊዜም ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ ልደተ ክርስቶስ ድረስ ያለው አሥራ አራት ትውልድ ይታሰባል። እረኛ የሌለው በግ ተኵላ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ምክንያት ከትጉህ እረኛው የተለየው የሰው ልጅም ሰብሳቢና የሚያሰማራ ጠባቂ እንዲኖረው ነቢያት ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ (መዝ፦፸፱፥፩) በማለት ይማፀኑ ነበር።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጊዜው ሲደርስ መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል" ዮሐ፣ 1011 በማለት መልስ ሰጥቷል። "እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም በለመለመ መስክ ያሳድረኛል መዝ፥(፳፪፦፩-፪) ተብሎ እንደተጻፈ በዚህ የጾም ወቅት አቤቱ ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፣ ቸሩ እረኛችን ሆይ ተቅበዝብዘናልና እባክህ አስበን፣ የቀዘቀዘው ፍቅራችንን መልስልን፣ አንተ እውነተኛ ሰላምህን ስጠን እያልን ምንም ወደ ማያሳጣን ወደ እውነተኛው እረኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ በንስሐ ልንመለስ ይገባል።

ወስብሃት ለእግዚአብሔር

/ ቀሲስ ሄኖክ ያሬድ