በኦርየንታል ኦርቶዶሳዊያን አብያተ ክርቲያናት ዘንድ ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ልዩ የክብር ሥፍራ የሚሰጣት በነገረ ድኅነት ውስጥ ታላቅ የሆነ ድርሻ ስላላት ነው። ስለሆነም የክርስትና ሕይወት በምልጃ አገልግሎት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ኦርቶዶክሳዊያን ምእመናንም እመቤታችን ባሕረምህረት ወደብረ ትዕግሥት ከሆነው አምላክ የተሰጣትን የምሕረት ቃል ኪዳን ፍጹም በማመን በጸሎቷና በምልጃዋ ዘወትር ይማጸናሉ። በዚህም መሠረት እናቱ ድንግል ማርያምን በዚህ ቃልኪዳን ያከበረው አምላክ ከመረጥኋዋቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ፤ “... ኪዳኔን አላረክስም፤ ከከንፈሬም የወጣውን አልለውጥም “(መዝ.፹፰፡፴፩-፴፬) ሲል ይጎበኘናል፤ በቸርነቱና በረድኤቱም ይጠብቀናል።

እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ሦስት ዓመት ከቤተሰቧ ጋር፤ አሥራ-ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፤ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀናት ጌታን ጸንሳ፤ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ጋራ፤ አሥራ አምስት ዓመት በወንጌላዊው በዮሓንስ ቤት ከኖረች በኋላ በስድሳ አራት ዓመቷ ጥር ሃያ አንድ ቀን አርፋለች። ስለ እመቤታችን እረፍትና ትንሣኤ በቅዱስ መጽሓፍ “አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦትም” በማለት በምሥጢር ይገልጸዋል። መዝ.፻፴፩፡፰

ነቢዩ ዳዊት ይህን ቃለ ትንቢት የተናገረው ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ ሲል ነው። ይህም እመቤታችን እንደ ልጇ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው። ታቦት ያላት ማደሪያው ስለሆነች ነው። የወላዲተ አምላክ ዜና እረፍቷን እና ትንሣኤዋን በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን እንደሚተረከው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት በሆነበት ዕለት፤ ሐዋርያት የእመቤታችንን አስከሬን ለማሳረፍ ወደ ጌቴ ሴማኒ መካነ ዕረፍት  (የመቃብር ቦታ) ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንዐት መንፈስ ተነሣስተው “ቀድሞ ልጇን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ በአርባኛውም ቀን ወደ ሰማይ አረገ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል” እያሉ በማስተማር ሕዝቡን ፈጽመው ወስደውታል። አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷንም እንደ ልጇ ተነሣች፤ ዐረገች እያሉ በማስተማር ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን? “ኑ! ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት” ብለው ተማክረው መጥተው ከመካከላቸው ታውፍንያ የተባለ ጎበዝ አይሁዳዊ ተመርጦ ሄዶ የእመቤታችንን አስከሬን የተሸከሙበትን አልጋ ሸንኮር ያዘ። የአልጋውን ሸንኮር በያዘ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሠይፍ ሁለት እጆቹን ስለቆረጣቸው ከአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ። ነገር ግን ታውፍንያ በፈጸመው ድርጊት ተጸጽቶ ወደ እመቤታችን ስለተማጸነ በኅቡዕ ተአምር የተቆረጡ እጆቹን እንደቀድሞው አድርጋ ፈውሳዋለች።

በዚያ ጊዜም መልአክ እግዚአብሔር የእመቤታችንን አስከሬን ከሓዋርያው ዮሓንስ ጋር ነጥቆ ወስዶ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው ቅዱስ ዮሐንስም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሐዋርያት ሲመጣ የእመቤታችን አስከሬን በገነት መኖሩን ነገራቸው። ሐዋርያትም የእመቤታችንን አስከሬን አግኝተው ለመቅበር በነበራቸው ምኞትና ጉጉት የተነሳ በነሐሴ ፩ ቀን ሱባኤ ጀምረው ሲጾሙና ሲጸልዩ ከሰነበቱ በኋላ በአሥራ አራተኛው ቀን (በሁለተኛው ሱባኤ መጨረሻ፟) ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ አስከሬን አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፤ በውዳሴና በጽኑ ምሕላ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ ዕረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት። የእመቤታችን የቀብር ሥነሥርዓት በተፈጸመ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል። በዚያ ጊዜም ትንሣኤዋን ሌሎች ሐዋርያት አይተው ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተበሳጭቶ “ፈቀዳ ይደቅ እምደመናሁ” ይለዋል። ማለትም በፊት የልጅሽን ትንሣኤ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ከማዘኑ የተነሳ ከደመናው ተወርውሮ ሊወድቅ ቃጣው። በዚህ ጊዜ እመቤታችን ከእርሱ በቀር ሌሎቹ ሓዋርያት ትንሣኤዋን እንዳላዩ ነግራው ቅዱስ ቶማስን አፅናናችው። ሄዶም ለወንድሞቹ ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራችው አዝዛው ለምልክት ምስክር ይሆነው ዘንድ የተገነዘችበትን ሰበኗን ሰጥታው ፈጽማ ወደ ሰማይ ዐርጋለች።

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም ሐዋርያት ወዳሉበት ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ “እመቤታችንን እኮ ቀበርናት።” ብለው ነገሩት። እርሱም አውቆ ምሥጢሩን ደብቆ “አይደረግም! ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንደምን ይሆናል?” አላቸው። “አንተ እንጂ፤ ቀድሞ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ። አሁንም አታምንምን?” ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ወደ እመቤታችን መካነ መቃብር ይዘውት ሄደው ሲያሳዩት መቃብር ቢከፍቱ የእመቤታችንን አስከሬን አጡት። ደነገጡም፤ በዚህ ጊዜም ቅዱስ ቶማስ “አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሥታ ዐርጋለች” ብሎ የሆነውን ሁሉ ከተረከላቸው በኋላ ለማረጋገጫ ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው። እነሱም ሰበኗን ለበረከት ቆራርጠው ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄደዋል።

በዓመቱ ትንሣኤሽን ቶማስ አይቶ እኛ እንዴት ይቅርብን ብለው ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምሮ ሱባኤ ገቡ። በሱባኤው መጨረሻም በነሐሴ በአስራ ስድስተኛው ቀን (ነሐሴ ፲፮) ቀን) ጌታችን የለመኑትን ልመና ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፤ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ (ረዳት) ቄስ፤ ቅዱስ እስጢፋኖስን፤ ገባሬ-ሠናይ (ዋና) ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ ሁሉንም ከአቆረባቸው በኋላ የእመቤታችንን ዕርገቷን ለማየት አብቅቷቸዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሐዋርያዊቷ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ  ክርስቲያናችን ሥርዓት ሠርታ ከሰባቱ አጽዋማት ተርታ አስገብታ ይህን ታላቅ የበረከትና የምሥጢር መግለጫ ጾም ትጾማለች።

በጽኑ ለሚፈልጉት ሁሉ የሚሰጠውን ለሚገባቸውም ተትረፍርፎ የሚገኘውን የእግዚአብሔር ጸጋ በረከትን ለማግኘት፤ ሐዋርያት ያዩትን ድንቅ ምሥጢር የእመቤታችንን ትንሣኤና ዕረፍት ለማየትና ከሐዋርያት አበው በረከት ለመሳተፍ ጌታችን “ደቂቅየ ልጆቼ” ይላቸው በነበሩት ሐዋርያት አምሳል ሕፃናትና ወጣቶች፤ ሴቶችና ወንዶች አረጋዊያንም የጾመ ፍልሰታን መድረስ በናፍቆት እየጠበቁ በየዓመቱ በጾም በጸሎት ያሳልፉታል።

በዚህ የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት መታሰቢያ (በጾመ ፍልሰታ) ወቅት ብዙዎች ከቤታቸው ተለይተው፤ በመቃብር ቤት ዘግተው፤ አልጋና ምንጣፍ ትተው፤ በመሬት ላይ ተኝተው ዝግኝ ጥሬ እፍኝ ውኃ እየቀመሱ በጾምና በጸሎት በመትጋት በታላቅ ተጋድሎ ይሰነብታሉ።

በአጠቃላይ በሰሙነ ፍልሰታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለው ሁኔታና ሕዝቡ ደግሞ ልጅ አዋቂ ሳይል የሚያሳየው ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ለእመቤታችን ያላቸውን ጽኑና ጥልቅ ፍቅር የሚያረጋግጥ ነው።

ከብርሃነ ትንሣኤዋ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፤

ወስብሐት ለእግዚአብሔር  ወለመስቀሉ ክቡር ወለወላዲቱ ድንግል

ከቤዛ ኩሉ ሰ/ት/ቤት ትምህርት ክፍል

በአቶ አበጀ ሐደሮ