በሀገራችን ኢትዮጵያ በሃይማኖት ታሪክ መዘክርነት ሲከበሩ ከሚኖሩ ዓመታዊ በዓላት አንዱ መሰከረም 10 ቀን የሚከበረዉ የአምላካችን የመድኃኒታችን የእየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ዕለት ሲሆን የተከተል ጽጌ በዓል ተብሎ ይከበራል። ይህ ሃይማኖታዊ በዓል በነበረዉ የመንግሥት አስተዳደር ለዉጥ ከ1966 ጀምሮ ለ20 ዓመታት ያህል ተቋርጦ ነበር። ከዚያም በ1986 በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዐውደ ምሕረት በመንፈሳዊ ሥነሥርዓትና ለምእመኑም ሆነ ለኅብረተሰቡ አበባ እየታደለ መከበር ጀምሮ እንደቀጠለ ነው።

አባታችን ብጹዕ አቡነ ገሪማ (ዶ/ር) ስለ ተቀጸል ጽጌ በዓል ጥንተ ምሥጥር እንደሚከተለዉ አስተምረዋል። ዐፄ ዳዊት በዘመነ መንግሥታቸዉ በ14ኛዉ ክፍለ ዘመን ፍጻሜ አካባቢ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ዕለት መሰከረም 10 ቀን ታላቅ የአቀባበል በዓል አድርግዉ ነበር። ለዚህም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይህ ዕለት “የዐፄ መስቀል” በዓል እየተባለ በቤተ ክህነት እና በቤተ መንግሥት ጥምረት “ተቀጸል ጽጌ ኢትዮጵያዊዉ ዐፄጌ” በማለት የቅዱስ ያሬድ  መዝሙር እየተዘመረ ሲከበር ኖሯል። ትርጉሙም “የኢትዮጵያ ንጉሥ ክረምቱ አልፎልሃልና አበባን ተቀዳጅ፣ አበባን ተላበስ” ማለት ነዉ። በዚያን ጊዜም ሴቱም ወንዱም ትልቁም ትንሹም አበባ በመያዝ በሆታና በዕልልታ የተቀጸል ጽጌን በዓል ሲያከብሩ እንደነበር ቅዱሳት መጻሐፍት (መጽሐፈ ድጓ) ያስረዳሉ።

ዐፄ ዳዊት ከሞቱ በኃላ የነገሡት ልጃቸዉ ዐፄ ዘረዐ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን በየረር፣ በመናገሻ ተራራ፣ ከዚያም በልዩ ልዩ ቦታዎች በማዘዋወር ቦታ ሲመርጡለት ቆይተዉ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” ሲተረጎም “መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ”  የሚል ሕልም በተደጋጋሚ አይተዉ ደብረ ብርሃን በታቦተ ኢየሱስ ሥም በተሠራዉ ቤተ ክርስቲያን ማኖራቸዉ ይነገራል። ከዚያም ቀድሞ ያዩትን ሕልም በተደጋጋሚ በማየታቸዉ ግማደ መስቀሉን በደቡብ ወሎ በአምባሰል አዉራጃ በግሸን ወረዳ ደብረ ከርቤ በተባለዉ ተራራማ ቦታ ላይ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን አሳንፀዉ መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱን በማክበር ወደ አሳነፁት ቤተ ክርስቲያን አስገቡ። ታቦቱ ያረፈበት የደብረ ከርቤ ተራራ አሻቅቦ ሲታይ የመስቀል ቅርጽ ያለዉ ሲሆን በቀድሞ ጊዜ የመሳፍንቱና የመኳንንቱ ልጆች ሥረዓት ንግሥና እና የቤተ መንግሥት አስተዳደር የሚማሩበት ነበር። ደብረ ከርቤ ነገሥታቱ እና ሕዝበ ክርስትያኑ በየጊዜዉ የሚጎበኙት እና የሚሳለሙት ታላቅ ደብር ሆነ።

ግሸን ደብረ ከርቤ

 

የተቀጸል ጽጌ በዓል የሚከበርበት ወረኃ መስከረም ክረምቱ አልፎ የመጸው (አበባ) ወቅት ስንቀበል ነዉ። በተለመደዉ የመስቀል መዝሙራችን “አበባ አበባዬ መስከረም ጠባዬ” እያልን የምድራችንን በልምላሜ መዋብ፡  አረንጓዴ መጎናጸፍ፣ በአበባ መድመቅ፣ ሰማይ በከዋክብት አጊጦና አሸብርቆ መታየቱን እያደነቅን የምናከብረዉ የተቀጸል ጽጌ በዓል ከወቅቱ የተስማማ ነው ማለት ይችላል። ይህ ብሩህ ወቅት ፍጹም የመንፈስ መታደስ የምናገኝበት እና አበባ እየተሰጣጣን መከባበርን እና ፍቅርን የምንገልጽበት የኦርቶዶከስ ቤተ ክርስቲያን አዘጋጅታ ያቆየችልን በዓል ሲሆን በዘመነ ኦሪት ይከበር ከነበረዉ በዓለ ሰዊት ወይንም የእሼት በዓል ሊነጻጸር ይችላል። አበባ መሰጣጣቱ ባለንበት አገር አሜሪካኖች የፍቅረኛሞች ቀን (valentine’s day) ብለዉ ከሚያከብሩት ያመሳስለዋል።

 

ከላይ በዝርዝር እንደተቀመጠዉ የተቀጽል ጽጌ በዓል ከዘመነ አበዉ ሲያያዝ የመጣ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተቀደሰዉን የግማደ መስቀሉን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ታሪክ የምናስብበት በዓል ነዉ። በሌላ በኩል በዚህ በዓል ቤተ ክርስቲያን ለሀገር መሪዎች መልካም ምግባር እሰየዉ በርቱ የምትልበት መሆኑ የሚያስደስት ሲሆን በጎነታቸዉን ቢቻ ሣይሆን ጉድለታቸዉንም አስተካክሉ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ይኑራችሁ ብላ ብትገጽጽ በዓሉን ፍጹም ክርስቲያነዊ ያደርገዋል።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣

ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን!

በዶ/ር ስሎሞን ፎሌ