እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ። ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ። (መዝሙር ፻፴፩፥፲፫-፲፬)

እስራኤል በግብፃውያን እጅ ወድቀው በግፍና በባርነት ሲገዙ ልዑል እግዚአብሔር አምላክ መገፋታቸውንና ስቃያቸውን ተመልክቶ ድንቅ በሆነ ተአምራቱ በግፍ ከሚገዟቸው የግፍ ሰዎች እጅ ታድጓቸዋል። በኦሪት ዘጸአት ከምእራፍ ሰባት እስከ ምእራፍ አሥራ-ሁለት ድረስ ታሪኩ ተጽፎ እንደሚገኘው አሥር መቅሰፍቶችን በፈርዖንና በግብፃውያን ላይ አድርሶ በሙሴ አማካኝነት ባሕር ከፍሎ አሻግሯቸዋል።

 እስራኤልም አምላካቸውን አውቀውና ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው እንዲኖሩ ታቦተ ጽዮንን ኃይሉን ባሳደረበት በሙሴ አማካኝነት ልኮላቸዋል። ለታቦቱ የሚያስፈልገው ሥርዓት ከተሠራ በኋላ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን ጽላት ሲያሳርፍበት የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን እንደሞላ (ዘጸ ፵፥፴፬) ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። እግዚአብሔርን ለሚወዱ እንደ ሐሳቡም ለተጠሩ ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን ተብሎ እንደተጻፈ የታቦተ ጽዮን በፍልስጥኤማውያን እጅ መውደቅና መማረክ የእግዚአብሔር ክብር እንዲገለጥና የታቦቱም ኃይል በማያምኑ ሰዎች ዙሪያ እንዲታይ ነው።

ታቦተ ጽዮን በፍልስጥኤማውያን እጅ ወድቃ ሳለ ዳጎን በተባለ ቤተ ጣዖታቸው ውስጥ አኑረዋት ነበር፡፡ ነገር ግን ዳጎን ማንም ሳይነካው በታቦቷ ኃይል ወድቆና ተሰባብሮ ተገኘ። ይኽ ሁኔታ ያሳሰባቸው ፍልስጤማውያን ታቦተ ጽዮንን ለመመለስ ግድ ሆነባቸው። አብረው ሊኖሩ የማይችሉ በመሆናቸውም ዳጎን ራሱ እየተቆረጠ እጁም እየተሰባበረ ወደቀ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? (፪ቆሮ ፲፮፥፮) እንዳለው የእግዚአብሔር ታቦትና ሰዎች የቀረጹት ጣዖት አብረው ሊኖሩ አልቻሉም።

የእግዚአብሔር ታቦት በመባል የምትታወቀዋ ታቦተ ጽዮን ባላት አስገራሚ ኃይል ዳጎንን ከመሰባበር ባሻገር ባሕረ ዮርዳኖስን ከፍላለች (ኢያሱ ፫፥፲፬-፲፯) ፤ የኢያሪኮን ቅፅር አፍርሳለች (ኢያሱ ፮፥፩-፳፩) ፤ ታቦቱን በድፍረት ሊነካ የሞከረውን ኦዛን ቀስፋለች (፩ሳሙ ፮፥፮) ፤ የአቢዳራን ቤት በበረከት ሞልታለች (፪ሳሙ ፮፥፲፬) ፤ ንጉሥ ዳዊት ለክብርዋ ዘምሮላታል (፪ሳሙ ፮፥፲፬) ፤ ጠቢቡ ሰሎሞንም በቤተ መቅደስ በክብር አኑሯታል (፩ነገ ፰፥፩)

ፈቃደ እግዚአብሔር በመሆኑም ታሪክዋ በአንደኛ ነገሥት ምእራፍ አሥር እና በሁለተኛ ዜና ምእራፍ ዘጠኝ እንደተጻፈው ጊዜው ሲደርስ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ጥበብ ለማየት እንደሄደች እና አስፈላጊውን እጅ መንሻ እንደወሰደችለት ታሪኩ ይነግረናል። በዚያው አንፃርም እርስዋም ከጠቢቡ ሰሎሞን እርሱ አስቦ ከሰጣት ሌላ የለመነችውን ሁሉ እንዳገኘች ቅዱስ መጽሐፍ በሁለቱም የመጽሐፍ ክፍሎች እንዲህ ሲል ይነግረናል፦

* ንጉሡም ሰሎሞን፥ በገዛ እጁ ከሰጣት ሌላ፥ የወደደችውን ሁሉ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ ለሳባ ንግሥት ሰጣት፤ እርስዋም ተመልሳ ወደ ምድርዋ ሄደች። ፩ነገ ፲፥፩-፲፫

* የሳባም ንግሥት ወደ ንጉሡ ካመጣችው የሚበልጥ፥ ንጉሡ ሰሎሞን የወደደችውን ሁሉ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ ሰጣት፤ እርስዋም ተመልሳ ከባሪያዎችዋ ጋር ወደ ምድርዋ ሄደች። ፪መጽ ዜና ፱፥፩-፲፪

ቅዱስ ዳዊት በታቦተ ጽዮን ፊት እየዘለለ ዝማሬን እንዳቀረበው ኢትዮጵያውያን ዛሬም ያለማቋረጥ ዕለት ዕለት በታቦተ ጽዮን ፊት በዝማሬ፣ በማኅሌትና በቅዳሴ ምስጋናቸውን ያቀርባሉ። ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር በመባል የምትታወቀው እግዚአብሔር ክብሩን የገለጸበትና ድንቅ ያደረገበት ታቦተ ጽዮን በአክሱም፣ ግማደ መስቀሉ በጊሸን መገኘታቸውና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ያለማቋረጥ ቃለ እግዚአብሔርን ከዓመት እስከ ዓመት ስለምታደርስበት ነው።

ቅድስት አገራችንን ኢትዮጵያን ለውዳሴ የመረጣትና ሕዝቦችዋም ያለማቋረጥ ዕለት ዕለት ምስጋና እንዲያቀርቡ ያዘጋጃቸውና ብርታቱን የሰጣቸው ልዑል እግዚአብሔር ስሙ የተባረከ ይሁን፤ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልመናና ጸሎት ዘወትር ከእኛ አይለይ።

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አብርሃም ሰሎሞን