ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የወላይታ ዳውሮና ኮንታ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በብፁዕ አቡነ ዘካርያስ የኒውዮርክ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ጋባዥነት በቤተ ክርስቲያናችን ተገኝተው ቡራኬ ሰጡ። ብፁዕነታቸው አርብ ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. ሚኒያፖሊስ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳዳሪ በመልአከ አርያም ቆሞስ አባ ኃይለ ሚካኤልና በቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ምእመናን አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን በቀጥታ ወደ ቤተ ክርስቲያናችን በማምራትም በዚያው ሲጠብቋቸው ለነበሩ ምእመናን ቡራኬና ትምህርት ሰጥተዋል።

በማግስቱ ቅዳሜም የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ዓመታዊ በዓል ዋዜማ ላይ በመገኘት "እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው" በሚል ርእስ ቡራኬና ትምህርት ሰጥተዋል። ትምህርታቸውንም በማያያዝ "ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ወጥተው በሄዱበት ሁሉ ከራሳቸው ቤት አስቀድመው የእግዚአብሔርን ቤት እንደሚሠሩ ሁሉ እናንተም ይህንን ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ከራሳችሁ ቤት አስቀድማችሁ በመሥራታችሁ ይኼው አባቶቻችሁን በራሳችሁ ቤትና በራሳችሁ ሰዓት ተቀብላችሁ ማስተናገድ ቻላችሁ፤ በዚህም እግዚአብሔርን ልታመሰግኑ ይገባች» ብለዋል። ብፁዕ አባታችን በሦስተኛው ቀን አገልግሎታቸውም ለቅዱስ ዮሐንስ ዓመታዊ የንግሥ በዓል ከማኅሌት አገልግሎት ጀምሮ ተገኝተው ምእመናኑንም ቀድሰው አቁርበዋል። በመቀጠልም "ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ" በሚል ዐቢይ ርእስ ሰፋ ያለ ትምህርትና ምክር ሰጥተዋል። በትምህርታቸውም "ስለ ስሙ የሚገዙትን እግዚአብሔር አምላክ ከሁሉም አብልጦ ይወዳልና ካህኑ ዘካርያስ እና ኤልሳቤጥ በእግዚአብሔር ፊት የነበራቸውን የጽድቅ ሕይወት አስበው እንዳዘኑና እንደተከዙ አረፍተ ዘመን እንዳይገታቸው በማለት በእርጅናቸው ዘመን በመልአከ ብሥራት "ከሴቶች ከተወለዱት መካከል እንደ እርሱ ያለ አልተነሳም" የተባለለትን እና ሲፀነስ የአባቱን አንደበት የዘጋውን፣ በማኅፀን ሳለ ለእመቤታችን የሰገደውን፣ ሲወለድ የአባቱን አንደበት የከፈተውን፣ በኋላም አምላኩን ያጠመቀውን መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ሰጣቸው" ብለዋል።

በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ መሆን ማለት አንዱ መገለጫው አዛውንትና ጎልማሶች ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን የሚቀበሉበትን፣ ሕፃናት እግዚአብሔርን በመፍራት የሚያድጉበትን፣ ወንጌል የሚስፋፋበትን ቤቱን መሥራት ነውና እናተም ይህንን ታላቅ ቤተ ክርስቲያን መሥራታችሁ በእጅጉ ያስመስግናችኋል፤ ስማችሁ

በዚህ በመቅደሱ እና በአርያም ባለች መዝገብም ተጽፎ ይኖራል ሲሉ አመስግነዋል። ይህን ሁሉ ከአደረጋችሁ በኋላ ግን እኛ በጥበባችን እና በገንዘባችን አደረግን ብላችሁ የምትመኩ ከሆነ በእግዚአብሔርና በእናንተ መካከል ያለው ድልድይ ይሰበርና ባላችሁበት መቅረት ብቻ እንጂ ማደግና መስፋት ስለማይኖር "እግዚአብሔር አደረገ!" ማለት ይገባችኋል ሲሉ ምእመናንን በአጽንዖት መክረዋል። አያይዘውም የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት ከመጠበቅና ከማጽናት አንጻር የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ ካህናት ትልቁን ኃላፊነት ሊወስዱ እንደሚገባቸውና “እግዚአብሔርን ሁልግዜም "እሺ!" እያለ የሚታዘዘውን ምእመን ላለማሳዘን በመደማመጥ፣ በመመካከርና እኔ ከሁሉ አንሳለሁ በሚል ትኅትና ልታገለግሉና የቤተ ክርስቲያኑን አንድነት በዘለቄታው የመጠበቅ ኃላፊነትን ልትወጡ ይገባል” ሲሉ ከአደራ ጋር ለአገልጋይ ካህናት አሳስበዋል።

በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ቅዱስ ፓትርያኩን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ቤተ ክርስቲያናችን ተገኝተው ሲባርኩን ስድስተኛው ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አባታችን አቡነ ማቴዎስ ሐምሌ ፭ ቀን የሚከበረውን የጴጥሮስ ወጳውሎስን በዓል በኪዳን ጸሎት ቤተ ክርስቲያናችን ተገኝተው አክብረውና ምእመኑን ባርከው ማክሰኞ ሐምሌ ፭/፳፻፰ ዓ.ም. ወደ ዋሽንግተን ዲሲ አምርተዋል።

እግዚአብሔር አምላክ ለብፁዕ አባታችን ረዥም የአገልግሎት ዘመን ከሙሉ ጤንነት ጋር እንዲሰጥልን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን!

ዘጋቢ አቶ ሠናይ ምንውየለት