በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም ወይረውዩ አድባረ በድው (በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ ጫካውም ስብን ይጠግባል፤ የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ። (መዝ. ፷፬፡፲፩)

አዲስ የሆነ ነገር መቼም ለማንም ተመልካች ደስ ያሰኛል። አዲስ ልብስ ምንም ዓይነት ዝቅተኛ ዋጋ ቢኖረውም ለለባሹም ለተመልካቹም የልቡና ደስታ ይሰጣል። አዲስ ዓመትም እንዲሁ ለሁላችን የደስታና የተስፋ ምንጭ ሆኖ ይታየናል። ይኽንን በመመልከት አባቶቻችን እና እናቶቻችን "እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ" የሚለውን ቃል በደስታና በመልካም ምኞት ሲለዋዋጡ ኖረዋል። "እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ እንዲሁም ለሚመጣው በሕይወት ያድርሳችሁ" የሚለውን መልካም ምኞት የተጎናጸፈውን ቃል በየመንገዱና በየቤቱ ሲነገር እንሰማዋለን፤ በካርዶችና በደብዳቤዎች ላይ ተጽፎም እናየዋለን። እነሆ ዛሬ አዲስ ዓመት እንደ ንጹሕ ብራና ተዳምጦ በፊታችን ተዘርግቷል። ይሁን እንጂ አዲሱን ዓመት ከመጀመራችን በፊት ያለፈውን ዓመት አንድ ጊዜ መለስ ብለን እንመልከተው፤ እንመርምረው። ልንሠራው የሚገባንን ሥራ ሠርተንበት እንደሆነ ልናዝን ልንጸጸት አይገባንም። አሁን ደግሞ ወደ አዲሱ ዓመት ፊታችንን መለስ አድርገን እንመልከት። በዚህ በሚመጣው ዓመት ልንሠራው ያሰብነው ነገር እንዳለ እንመርምር። አንድ ነገርን ከመሥራታችን በፊት ማሰብ አስፈላጊ ነው። ማሰብ ካልቻልን መሥራትም አንችልም። ነገር ግን በጥሩ ያሰብነውን ሐሳብ በሥራ ላይ ለማዋል ጊዜ ያስፈልጋል። ማናቸውም ሥራ የሚሠራው በጊዜ አማካኝነት ነው። ጊዜ ከሌለ ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት አንችልም።አዲስ ዓመት እንደ ንጹሕ ወረቀት ሆኖ በፊታችን ተዘርግቷል። ጥሩ አድርጎ የመጻፍ ጉዳይ የእኛ ፈንታ ነው። በዚህ በአዲሱ ዓመት በአገራችን ውኆች ድፍርስነታቸውን አስወግደው እንደ መስተዋት ጠርተው ይታያሉ። መንገዶች በላያቸው ላይ ወድቆ የነበረውን አፈሩን ደለሉን አስወግደዋል። ሰማይ በደመና ተሸፍኖ መልኩን አጥቁሮ ቁጣውን አበርክቶ ነበር። አሁን ግን በከዋክብት አጊጦና አሸብርቆ ፊቱን በፈገግታ ሞልቶ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ተዘጋጅቷል። ተራሮች ኮረብቶች ራቁታቸውን ሆነው በጉምና በጢስ ተሸፍነው ከርመው እነሆ አዲሱን ልብሳቸውን ለብሰው በአበቦች ተሸፍነው በሰልፍ ቆመው ሲታዩ እጅግ ያስደስታሉ፤ ልምላሜያቸውም ሰውነትን ያድሳል፤ መዓዛቸውም አእምሮን ይመስጣል። እኛስ ይኼንን አዲስ ዓመት ለመቀበል ምን ያህል ዝግጅት አድርገናል? እንደ ሥነ ፍጥረቱ በንጽሕና፣ በቅድስና፣ በትሕትና፣ በየዋህ ልቡና አጊጠናል? ወይስ ልቡናችን በቂም በተንኮል በምቀኝነት ይገኛል? ሥነ ፍጥረትን አብነት አድርገን ሥነ ፍጥረትን ተከትለን ያለፈው አሮጌ ዓመት በላያችን የጣለውን ደለል አራግፈን ጥለን ባልንጀራችንን በማፍቀር የተጣላነውን ታርቀን፤ የበደልነውን ክሰን የቀማነውን መልሰን እንደ አደይ አበባ አብበን አሸብርቀን አዲሱን ዓመት መቀበል ይኖርብናል። ይኽንን በማድረግ የተቀበልነው እንደሆነ ይኸ ዓዲስ ዓመት በእርግጥ የስሙን ትርጓሜ ለማግኘት ይችላል ማለት ነው። እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አሸጋገረን።  ልዑል አምላካችን አዲሱን ዓመት የበረከት፣ የፍቅር፣ የሰላም ያደርግልን ዘንድ ቅዱስ ፍቃዱ ይሁንልን።

መልአከ አርያም ቆሞስ አባ ኃይለሚካኤል