ልብ የደም ስሮችና የልብ በሽታ ምንድን ነው?

ለልብ የደም ስሮችና ልብ በሽታ (Coronary artery disease) ምክንያት የሚሆነው የስብና የኮሌስተሮል ቅሪት (Plaque) በመባል የሚታወቀው ንጥረ ነገር ወደ ልባችን ደም በሚያመላልሰው የደም ስሮች ውስጥ መጠራቀም ሲጀምርና ሲገነባ ነው። ይኽ የስብና የኮሌስተሮል ቅሪት ወይም ንጥረ ነገር የሚፈጠረው ከስብ (ኮሌስተሮል) ጥርቅም ሲሆን የሚከማቸውም በደም ማመላለሻ ቱቦ ውስጥ ነው። ይኽ ሁኔታ ሲከሰት የደም ማመላለሻ ቱቧችን እየጠበበ ይመጣል። ይኽም ሂደት የደም መመላለሻዎች መጠጠርና መጥበብ (atherosclerosis) በመባል ይታወቃል።.

በደም ማመላለሻ ቱቦ ውስጥ የስብና የኮሌስተሮል ቅሪት ወይም ንጥረ ነገር  መጠራቀምና ማደግ ወደ ልብ ጡንቻ ውስጥ በቂ የሆነ ደም እንዳይደርስ ያደርጋል። ይኽ ደግሞ ለልብ የደም ስሮችና የልብ  በሽታ (Coronary artery disease) ዓይነተኛ ምልክት ነው። በልብ ውስጥ በቂ ደም ያለመኖሩ ሁኔታ ከባድ የሆነ የደረት ሕመም እና መታወክን ያስከትላል፤ እየቆየም የልብን ጡንቻዎች ያዳክማል። እነዚህ ሁኔታዎች ከፍተኛ የሆነ ችግር በመፍጠር የልብ ድካም ከማምጣታቸው ባሻገር ልብ በተገቢው መጠን ሊረጨው የሚገባውን ደም እንዳይረጭ ያደርጉታል፤ ያልተስተካከለና የተዛባ የልብ ምት እንዲኖርም ያደርጋሉ።

ለአንዳንድ ሰዎች የልብ የደም ስሮችና የልብ በሽታ (Coronary artery disease) (CAD) የመጀመርያ ምልክት የሚሆነው ድንገተኛ የልብ ሕመም (heart attack) ነው። ድንገተኛ የልብ ሕመም ሊመጣ የሚችለው  የስብና የኮሌስተሮል ጥርቅም/ቅሪት (Plaque) በመባል የሚታወቀው ንጥረ ነገር ወደ ልብ የሚመጣውን የደም ማመላለሻ/የደም ስሮች ሙሉ ለሙሉ ሲዘጋው ወይም የተጠራቀመው ቅሪት በገሚስ ተሸርፎ በመጓዝ የልብ ደም ስሮች ውስጥ መርጋት ሲጀምር ነው።

በልብ የደም ስሮችና በልብ በሽታ እንደታመምኩኝ በምን አውቃለሁ?

የልብ የደም ስሮችና የልብ በሽታ (Coronary artery disease) (CAD) እንዳለብዎት ወይም ለዚህ በሽታ እንደተጋለጡ የሚታወቀው ዶክተሮች የደም ግፊት፣ በሰውነት ውስጥ ያለውን የቅባት መጠን (ኮሌስተሮል) ፣ የስኳር ምርመራ ካደረጉ እና ቤተሰብዎት የልብ ሕሙማን መሆናቸውን ካጠኑ በኋላ ነው። ለበሽታው ክፉኛ የተጋለጡ ከሆኑና ዶክተሮቹ አንዳንድ ምልክቶች ካዩ ሌሎች ተጨማሪ ምርመራዎችን በማድረግ የበሽታው ተጠቂ መሆንዎትን ያረጋግጣሉ።

የልብ የደም ስሮችና የልብ በሽታን እንዴት ማከም ይቻላል?

የዚህ በሽታ ተጠቂ ከሆኑ ድንገተኛ የልብ ሕመምን(heart attack) እና እየተባባሰ ሊመጣ የሚችለውን አስከፊ የልብ ሕመምን ለመቀነስ  የሚወሰዱ አስፈላጊ እርምጃዎች አሉ። ምናልባት ዶክተርዎ ሕይወትዎን ሊለውጥ የሚችሉ ነገሮችን ሊያዙልዎት ይችላሉ። ይኸውም ጤነኛና

የተመጣጠነ ምግብ መብላት፣ በቂ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ እና ሲጋራ አለማጨስ ናቸው። መድኃኒትና የሕክምና ክትትልም አስፈላጊ ነው። መድኃኒት መጠቀም የልብ የደም ስሮችና የልብ በሽታን (Coronary artery disease) (CAD) ሊያመጡ የሚችሉትን እንደ ኮሌስተሮል፣ ደም ግፊት፣ የተዛባ ልብ ምት እና ዘገምተኛ የደም ዝውውርን (ስርጭት) መግታት ያስችላል። ለአንዳንድ ሁኔታዎች ከፍተኛ ሕክምና እና ቀዶ ጥገና ማድረግ ወደ ልብ መድረስ የሚገባውን ደም በበቂና በትክክለኛው መጠን እንዲደርስ ያስችለዋል።

ለልብ ሕመም አስጊ የሆኑ ዐበይት መነሻዎች ምንድን ናቸው?

ለልብ ሕመም አስጊ የሆኑ ዐበይት ጉዳዮች በሦስት ይመደባሉ፦

፩- ቀደም ብለው ያሉ በሽታዎች (የታማሚው ሰው የሰውነቱ የጤና)

፪- ፀባይ (የታማሚው ሰው የአመጋገብ ሁኔታ እና አኗኗሩ)

፫- ከቤተሰብ ውርስ ሊመጣ የሚችል በሽታ 

፩ኛ- የታማሚው ሰው የሰውነቱ የጤና ሁኔታ፦

በደም ውስጥ ያለው የኮሌስተሮል መጠን

ኮለስትሮል በጉበት ውስጥ ወይም በተወሰኑ የምግብ ዓይነቶች አማካኝነት የሚዘጋጅ ቅባትነት ያለው ንጥረ ነገር ነው። ይኽ ቅባትነት ያለው ንጥረ ነገር ለሰውነታችን አስፈላጊ ነው። ጉበታችንም ለሰውነታችን የሚያስፈልገውን መጠን ያህል ያዘጋጃል። የኮሌስተሮል መጠን አመጋገብና  ኮሎስትሮል ከአስፈላጊነቱ በላይ ለሰውነታችን ጥቅም አለመመጣጠን የተነሳ የኮሌስተሮል ክምችት ይፈጠራል - ይኽም ትርፍ ኮሌስተሮል ወደ ልባችን ደም በሚያመላልሰው ቱቦ ውስጥ ይከማቻል ወይም ይለጠፋል። ይኽ ሁኔታም የደም ማመላለሻ ቧንቧዎች ያጠባል፤ ለልብ ሕመምና ለተለያዩ ውስብስብ የጤና ቀውስ ያጋልጣል።

አንዳንድ ኮሌስተሮል"ጥሩ" እና "መጥፎ" በመባል ይታወቃል። ከፍተኛ ክብደት ያለው high–density lipoprotein cholesterol, or HDL, "ጥሩ" ተብሎ ይመደባል። ይኽም የልብ ሕመምን ለመከላከል ያስችላል። በአንፃሩም ዝቅተኛ ክብደት ያለው low–density lipoprotein, or LDL,  "መጥፎ" በመባል ይታወቃል። ይኽኛው ደግሞ ለልብ ሕመም ያጋልጣል። እነኝህን ለማወቅ የተለያዩ ኮሌስተሮል ዓይነቶችን ለመለካት ይቻላል።

ከፍተኛ የደም ግፊት

ለልብ ሕመም ሌላው ዐቢይ መነሻ የሚሆነው ከፍተኛ የደም ግፊት ነው። ይኽም ሁኔታ የሚከሰተው በደም ማመላለሻ ቱቦ ውስጥ የደም ግፊት ከፍተኛ ሆኖ ሲገኝ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ለከፍተኛ የደም ግፊት ምንም ዓይነት የሚታወቅ ምልክት አይኖረውም። የአኗኗር ሁኔታን በመለወጥ እና ሕክምና በመከታተል የደም ግፊትን መቀነስ፣ የልብ ሕመምን እና ድንገተኛ የልብ ሕመምን (Heart Attack) እድል ዝቅ ማድረግ ይቻላል።

Tserha Aryam Faith Community Nurse Program

ጽርሐ አርያም የእምነት ማኅበረ-ሰብ የጤና አገልግሎት

(ይቀጥላል)