አምድ ማለት ምሰሶ ማለት ሲሆን በቁሙ ስንገልጽው የአንድ ቤት ጣሪያ ወይም የቤቱ ምሰሶ ብለን የምንጠራው እና ቤቱ እንዳይዘም ወይም ወደ አንድ ጎን እንዳያዘነብል፤ ሚዛኑን እና ልኩን ጠብቆ እንዲቆም የሚያደርግ ነው። አዕማድ ስንልም ምሰሶዎች (ለብዙ)ማለት ነው ። ቤት በአምድ (በኮለም) እንደሚጸና ሃይማኖትም በእነዚህ አዕማደ ምሥጢራት ተጠቃሎ ይገለጻል፤ ምዕመናንም እነዚህን ምሥጢራት በመማር ጸንተው ይኖራሉ ።

ምሥጢር ማለት ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ በተወሰኑ ሰዎች ብቻ ተጠብቆ የሚቆይ ጉዳይ ሲሆን፤ አእማደ ምሥጢር ስንልም በሚታዩ ምሳሌዎች የማይታየውን የሃይማኖት ምሥጢር መረዳት፤ በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ ማግኘት ማለት ነው።

አምስቱ አእማደ ምሥጢር የምባሉት፡-
) ምሥጢረ ሥላሴ፦የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የምንማርበት 
፪) ምሥጢረ ሥጋዌ፡ የአምላክን ሰው መሆን የምንማርበት 
፫) ምሥጢረ ጥምቀት፡ ስለ ዳግም መወለድ የምንማርበት 
፬) ምሥጢረ ቁርባን፡ ስለ ክርስቶስ ሥጋና ደም የምንማርበት 
፭) ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን፡ ስለ ዳግም ምጽዓት የምንማርበት ናቸው ።


አምስቱ አዕማደ ምሥጢር በአፈጻጸማቸው በሦስት ይከፈላሉ ። 
) ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌ አምነን የምንቀበላቸው፤
፪) ምሥጢረ ጥምቀትና ምሥጢረ ቁርባን አምነን የምንተገብረው፤
፫) ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን አምነን በተስፋ የምንጠብቀው።

እነዚህን ምሥጢራት በቅደም ተከተል እንመለከታለን፤

) ምሥጢረ ሥላሴ

ሠለሰ ሦስት አደረገ፤ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ፤ ሥላሴ ማለት ሦስትነት ማለት ነው ። ምሥጢረ ሥላሴ ስንልም የአምላክን አንድነት እና ሦስትነት ማለታችን ነው። 

ሥላሴ በስም፤ በአካል፤ በግብር ሦስት ናቸው ብንልም በመለኮት፤

በህልውና፤ በባሕርይ፤ በእዘዝ በአገዛዝ በመሳሰሉት አንድ ስለሆኑ

አንድ አምላክ ተብሎ ይታመናል ይጠራል እንጅ ሦስት አማልክት አይባልም። ከዚህም የተነሣ ሥላሴ ሦስት ሲሆኑ አንድ፤ አንድ ሲሆኑ ሦስት በመሆናቸው ምሥጢር ተባለ። ይህም ለሚያምን ብቻ የሚገለጽ ምሥጢር ነዉ።

¨ በሥም፡- አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ (ማቴ. ፳፰፡፲፱)

¨ በግብር፡- አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ ነው። (ዮሐ. ፲፬፡፳፭)

¨ በአካል፡- ለአብ ፍጹም አካል፣ ለወልድ ፍጹም አካል፣ ለመንፈስ ቅዱስ ፍጹም አካል አለው (ማቴ. ፫፡፲፮)

የምሥጢረ ሥላሴን ትምህርት የጀመረው ራሱ እግዚአብሔር ነው።

መጀመሪያ አዳምን ሲፈጥረው ሰውን እንፍጠር በመልካችን እንደ ምሣሌያችን ብሏል (ዘፍ. ፩፡፳፮)። እነሆ  በዚህ አንቀጽእንፍጠር በመልካችን እንደ ምሣሌያችን” የሚለው ንግግር የሁለት የሦስት ተናጋሪዎች እንጂ የአንድ ተናጋሪ ቃል አይደለም። በመቀጠልእግዚአብሔር አምላክም አለ እነሆ አዳም ከኛ እንደ አንዱ ሆነ” (ዘፍጥረት ፫፡፳፪)። ስለዚህ እግዚአብሔር ከኛ እንደ አንዱ ሆነ በማለቱ ሦስትነቱን ያስረዳል።

እግዚአብሔርም አለ እንውረድ ቋንቋቸውንም እንደባልቀው አንዱ የባልንጀራውን ነገር እንዳይሰማ” ብሏልና። (ዘፍጥረት ፲፩፡፯) እነሆ በዚህ አንቀጽ እግዚአብሔር እንውረድ” ብሎ በመናገሩ ከሁለትነት የተለየ ሦስትነትን ያስረዳል። መረጃውም ሦስት ተናጋሪዎች በአንድ ቦታ ሆነው ሲነጋገሩ ሦስተኛው ሁለቱን እንውረድ” ሊላቸዉ ይችላል። ሁለት ሆነው ግን አንዱ ሁለተኛውን እንውረድ” እንጂ እንውረድ” ሊለዉ ስለማይችል ነዉ።

ከዚህ በላይ የተጠቀሱት የእግዚአብሔር ቃላት ተገልጸው ሲተረጎሙ አካላዊ ልባቻው አብ፤ አካላዊ ቃሉ ወልድ እና አካላዊ ሕይወቱ (እስትንፋሱ) መንፈስ ቅዱስን ሰውን እንፍጠር በመልካችን እንደ ምሳሌያችን ብሎ እንዳነጋገራቸዉ ይታወቃል።

የእግዚአብሔር የአንድነቱ እና የሦስትነቱ ማስረጃ ሁነው የታመኑ እነዚህ ሦስት ቃላት ከአንድ የበዙ ተናጋሪዎች ቃላት መሆናቸው ይታወቃል። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህም በሌላ አንቀጽ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን አይቶት እንዲህ ይላል፦ዖዝያን ንጉሥ በሞተበት ዓመት እኔ እግዚአብሔርን ከፍ ባለ በረጅም ዙፋን ተቀምጦ አየሁት፤ ሱራፌልም ከርሱ በላይ ቁመው ነበር። አንዱም ለአንዱ እንዲህ ሲሉ ይጮኹ ነበር፦ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር የሠራዊት ጌታ ምድር ሁሉ ምስጋናውን ሞልታለች (ኢሳ. ፮፡፩-፫)።

“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ፤ በአብ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸውም” ሲል ራሱን አብን እና መንፈስ ቅዱስን በመግለጽ ከሦስት አካላት ያልበለጠ ከአንድ አካልነት የወጣ ከሦስት አካላት ያልበዛ ሦስት ብቻ መሆኑን አስረድቷል። (ዮሐ. ፲፭፡፳፮፤ ማቴ. ፳፰፡፲፱)።  

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን!

በሊቀ ስዩማት ቀሲስ ዓለማየሁ አሰፋ