ክፍል 2- - ካለፈው የቀጠለ

የጽሑፉ ዓቢይ ነገር የሚያወሳው የሐዋርያትን ሥራ ሲሆን በይበልጥ አጉልቶ የሚናገረው ግን ሐዋርያት በወንጌል ያደረጉትን ተጋድሎና የተጓዙበትን ውጣ ውረድ፣ ለወንጌል የከፈሉትን  መሥዋዕትነትና የፈጸሙትን ተአምራት ነው። ከቃሉ መነሻነት እንደምንመለከተው ሦስት ዋና ነገሮች እናገኛለን ካለ በኋላ ሦስቱ ነጥቦች፦

           ፩)        ለአባቶች የተሰጠው ተስፋ              

           ፪)         የምስራች 

፫) ለእናንተ እንሰብካለን

የሚሉት መሆናቸውን ገልጾ "ለአባቶች የተሰጠው ተስፋ" እና "የምስራች" የሚለው ክፍል ተብራርቶበታል። ዛሬ ደግሞ "የምስራች" ተብሎ ከቀረበው የቀረውንና ሦስተኛውን "ለእናንተ እንሰብካለን" የሚለውን የመጨረሻ ክፍል እናቀርባለን፦

ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም “በእንተ ሔዋን ተዐፅወ ኆኅተ ገነት ወበእንተ ማርያም ድንግል ተርኅወ ለነ።” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በሔዋን ምክንያት የተዘጋው የገነት ደጃፍ በድንግል ማርያም ተከፈተ፤ ወደ ገነት ተመለስን። ሔዋን የሞት ምክንያት የሚሆነውን  ቃኤልን ወለደች ድንግል ማርያም ግን  የሕይወት ምግብና መጠጥ የሚሆነውን፣ የሞት ጻዕርን የሚያጠፋውንና የባርነት ቀንበርን የሚሰብረውን መድኃኒት የሆነውን  ኢየሱስ ክርስቶን ወለደች። የምሥራች ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከባሕርይ አባቱ ከአብ የተወለደው ድኅረ ዓለም ያለ አባት ከድንግል ማርያም የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለዚህ ነው እንግዲህ ሐዋርያት አበው "የምሥራቹን ወንጌል እንሰብካለን" ያሉት። ወንጌል ሕይወታችን የተቀየረበትና የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ሕልውናን በደንብ የተማርንበት፣ የጌታን የምሕረትና የፍቅር ሕግ ያወቅንበትና የተረዳንበት፣ ታሪካችን የተቀየረበት፣ የብሉይ መርገፍነት ተፈጽሞ የአዲስ ውል የተፈጸመበትና የእግዚአብሔር ወልድን ልዩ ፍቅር በመስቀል ያየንበት ስለሆነ እንማረዋለን፤ እናስተምረዋለን፤  ለዓለም ሁሉ እናውጀዋለን ።

 

፫) ለእናንተ እንሰብካለን

ወንጌል መፈጸሙን ላመናችሁ መጽናኛና ሕይወታችሁን ማደሻ የሚሆነውን በሁለት ወገን የተሳለውን ሰይፍ ለእናንተ  እናስተምራለን፤ እናሳውቃለን፤ እናስረዳለን። ላለፉት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ለምታምኑት በሐዋርያት አባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምሥራቹን ለእናንተ እንሰብካለን። ከዚህ ዋናው  የምንመለከተው የተያያዘ ታሪክ አንዱ የአንዱን ሳያናንቅ ያለፈውንም ያለውንም  የሚመጣውንም  እንደያዙ እንመለከታለን።  የነቢያቱ ትንቢት ቢፈጸምም ሐዋርያቱ ግን  ቅድመ ታሪኩን፣ ተስፋውን፣ ሂደቱን ሁሉ ለሕዝቡ በማሳወቅ ሂደቱን አያይዘው ኦሪት ለወንጌል መርገፍነቷን  ለአባቶች የተሰጠውን  ተስፋ  በሚገባ አስተላልፈዋል። አሁን  በዘመናችን ግን  አንዱ የአንዱን እያጣጣለ፣ አንዱ የሠራውን  አንዱ እያፈረሰ፣ አንዱ ጥሩ ያለውን ሌላው መጥፎ እያለ በማጣጣልና በመለያየት ስለ አንዲቷ ቤተ ክርስቲያን እየመሰከሩ አንዱ ሲያወግዝ ሌላው ሲፈታ አንዱ የፈታውን ሌላው ደግሞ ሲያወግዝ ይታያል። ግን ለምን? እኛ አዲስ መሠረት መሥራቾች ሳንሆን በተመሠረተው ላይ በማነጽ የምንኖር ነንና

አበው ያቆዩልን  ሥርዓት፣ ዶግማና ቀኖና ምንም ሳንሰርዝና ሳናጎድል ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል። እውነት ለመናገር  .በምናደርገው የመንፈሳዊ ውጣ ውረድ፣ የሐሳብ ልዩነትና የአመለካከት ልዩነት አይኖርም ማለት አይደለም። ግን ታላቂቱን ቤተ ክርስቲያንን በመመልከት የግል ሐሳባችንን እና የሰይጣንን አሠራር በመንፈሳዊ እይታ አይተን አጥብቀን ልንበረታ ይገባል። በፍጹም አምልኮት ተጠብቃ እዚህ የደረሰችዋን ቤተ ክርስቲያናችንን ከውስጥ ጠላቶች ተሐድሶያውያን እና ከጥቅመኞች፤ ከውጪ ደግሞ ከመናፍቃን ልንጠብቅ ያስፈልጋል።

 

ዛሬ በዘመናችን በተለይ ከውስጥ ሆነው የቤተ ከርስቲያንን አስተምህሮዋን፤ ዶግማዋን፤ ቀኖናዋን እና ሥርዓቷን እናድሳለን ብለው የተነሡ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ነቀርሳዎች የገሀነም ደጆች የማይችሏትን ለማፍረስ በብርቱ እየንተቀሳቀሱ ስለሆነ መምህራኖቻችንንና ካህናቶቻችንን ጠንቅቆ ማወቅ የቤተ ክርስቲያናችንንም አስተምህሮ በደንብ ቀርቦ መረዳት ያስፈልጋል። በርግጥ ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን ትልቁ ጊዜያችንን በመሻማት ሕይወታችንን ተስፋ በማስቆረጥ እንድንዝል፣ እንዳንበረታና  እንድንደክም፣ ከቆምንበት እንድንቀር፣ ከወደቅንበት ኃጢአት እንዳንነሳ እና ከዛለው ሀሳባችን  እንዳንመለስ ይታገለናል ። በዚህ አኳሃን እንኳን እኛን ታላላቅ የምንላቸውንም ፈትኗል፤ ለማሸነፍም ታግሏል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእስያ ስለደረሰብን መከራ ወንድሞች ሆይ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና ስለ ሕይወታችን እንኳን ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከአቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር። ፪ ቆሮ. ፩፡፰  እንዳለው።  ደግሞም እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈልን ለእነዚያ ደግሞ እንደተነገረ ለእኛ የምስራች ተሰብኮልናልና። ዕብ. ፬፡፪. ስለዚህ ተስፋችንን አለምልመን በመንፈሳዊ ሕይወታችን በርትተን በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ጸንተን ለመኖር አምላካችን ይርዳን ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለመስቀሉ ክቡር

መጋቢ አዕላፍ /ቀሲስ/  ስንታየሁ ደምስ (Bth.)

ሚያዝያ ፳፩/፳፻፰ ዓ.ም.